የዚምባቡዌ ፖሊስ አዲስ ሃይል ሊያቋቁም ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 17/2010)የዚምባቡዌ ፖሊስ አዲስ ሃይል ሊያቋቁም መሆኑን አስታወቀ።

አዲስ የሚቋቋመው ሃይል ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ጾታና ከለርን ሳይለይ  ፈጣንና ሙያዊ በሆነ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ ሃይል ነው።

ይሄ ሃይል ቀደም ሲል የዜጎችን የሰብአዊ መብት በመጣስና የገዢዎችን እድሜ ለማራዘም አላግባብ የሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽማል በሚል ሲወገዝበት የቆየውን ስሙን ይቀይረዋል ተብሏል።

በዚምባቡዌ ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ሃይሉ ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ ናቸው።

ለገዢው ፓርቲም ወግኗል በሚል ወቀሳዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል።

አሁን ላይ ታዲያ ይህንን ወቀሳ ያስቀራል የተባለና ጥያቄዎችን በአግባቡ የሚያስተናገድ ብሎም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ሃይል ማቋቋሙን የዚምባቡዌ ፖሊስ አስታውቋል።

የሃገሪቱ ፖሊስ እንዳስታወቀው ከሆነ የሚቋቋመው ሃይል በዋናነት ሲቋቋም በሃገሪቱ የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ነው።

ከዚህ ቀደም በስልጣን ላይ ላለው መንግስት በማገልገል የሚታውቀው የፖሊስ ሀይል አሁን ግን ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንደሚሰራ ማስታወቁን ነው አፍሪካ ኒውስ የዘገበው።

በሮበርት ሙጋቤ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሲመራ የነበረውና በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚታውቀው የዚምባቡዌ ፖሊስ ከአሁን በኋዋላ እንደቀድሞው አይሰራም ተብሏል።

አሁን ዚምባቡዌን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ኢመርሰን ማንጋግዋ ስልጣን ከያዙ በሁዋላ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሚያካሄድ መግለጻቸውን ተከትሎ የተወሰደ ርምጃ ሊሆን እንደሚችል ነው ዘገባው ያመለከተው።

የዚምባቡዌ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና የአለም አቀፍ የንግድ ሚኒስተር ሱቢሱሶ ሞዮ ለንደን መሰረቱን ላደረገው ተቋም አንዳሉት በመጪው ምርጫ ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ኢመርሰን ማንጋግዋ እራሳቸውን ስልጣን ለመልቀቅ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

አክለውም ግለሰቦች ይለዋወጣሉ ሀገር ግን ነዋሪ ናት ማለታቸውን ዘገባው ገልጿል።

ኢመርሰን ማንጋግዋም ምርጫውን ካላሸነፉ ቦታውን ለመልቀቅ ፍላጎት ማሳየታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

የፖሊስ ሀይሉም በቀጣይ ከፍትህ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩና ህጋዊ ያልሆነ ማንኛውንም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለፍርድ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።