(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 8/2010) ግብጽ በአባይ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስታት ያወጧቸውን መግለጫዎች ውድቅ አደረገች።
ግብጽ የተቋረጠው ውይይት በካይሮ እንዲቀጥል ብትፈልግም ጥሪውን አሁን ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆነች የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጿል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በአባይ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ በካርቱም የተካሄደው የኢትዮጵያ፣የሱዳንና የግብጽ ውይይት የተቋረጠው በግብጽ ችግር ምክንያት አይደለም።
እናም ኢትዮጵያና ሱዳን የውይይቱን መቋረጥ አስመልክቶ ያወጡት መግለጫ ግብጽን መውቀሱ ትክክል አይደል ብሏል።
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ አቡ ዛይድ እንዳሉት የሀገራቸው መንግስት በቴክኒካዊ ጉድዮች ላይ ስምምነት እንዲደርሱ አዎንታዊ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
በጉዳዩ ላይ ከስምምነት እንዲደረስም ግብጽ ተለሳልሳ መቅረቧን ነው የተናገሩት።
ግብጽ የአለም ባንክ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋም የዚሁ አወንታዊነት ማሳያ ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ይህም ሆኖ ግን በግብጽ፣በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል በካርቱም የተካሄደው ውይይት ያለፍሬ መበተኑን ገልጸዋል።–ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይገልጹም።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለሰ አለም ግን ግብጽ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጠር በ1959 የነበረውን የሱዳንና የግብጽ ስምምነት እውቅና እንዲሰጠው በመጠየቋ ውይይቱ መክሸፉን ይፋ አድርገዋል።
እናም ግብጽ ውይይቱ በካይሮ እንዲቀጥል ብትፈልግም የኢትዮጵያና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ውይይቱን በቅርቡ ለመቀጠል ፍላጎት የላቸውም ብለዋል።