አቶ ታዬ ደንደአ፣ስዩም ተሾመና ኢያሱ አንጋሱ ከወህኒ ወጡ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 8/2010)ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት መምህር ስዩም ተሾመና አቶ ታዬ ደንደአ ዛሬ ከወህኒ ቤት ወጡ።


የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ኢያሱ አንጋሱም ከወህኒ መፈታታቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በጽሑፍ እንዲሁም በውውይትና በቃለ ምልልስ በንቃት የሚሳተፈው መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ታዬ ደንደአ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ኢያሱ አንጋሱ ከወህኒ የወጡት በዛሬው ዕለት ነው።
አቶ ታዬ ደንደአ በሞያሌ ከተማ የመከላከያ ሰራዊቱ የፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ ምልልስ ግድያው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው በማለት ድርጊቱን ማውገዛቸው ይታወሳል።
አቶ ታዬ ደንደአ በመብት ተሟጋችነታቸው በአጠቃላይ ከ10 አመታት በላይ በወህኒ ያሳለፉ መሆናቸው ተዘግቧል።
በዚህም የተነሳ የ4 አመት የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ 15 አመታት ያህል የፈጀባቸው እንደሆነም በእሳቸው ዙሪያ ከተሰሩ ሪፖርቶች መረዳት ተችሏል።
የአምቦ ዩኒቨርስቲው መምህር አቶ ስዩም ተሾመ በመብት ተሟጋችነቱ የሚታወቅ ሲሆን ፣በዚህም በመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታሰረ ሲሆን በሁለተኛውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታስሯል።


የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አንዱ የሆኑት ኮለኔል ኢያሱ አንጋሱን ጨምሮ ሶስቱም እስረኞች ዛሬ ከወህኒ መፈታታቸው ታውቋል።