89 በመቶው ትምህርት ቤቶች ከዓለም አቀፍ መመዘኛ በታች መሆናቸውን የትምህርት ሚንስቴር ጥናት አረጋገጠ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ/ም) ተማሪዎችና መምህራን በቋንቋ መግባባት ተቸግረዋል
በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት የጥራት ደረጃቸው አጠያያቂ ደረጃ ላይ መድረሱን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተካሄደው አምስተኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥራት ጉባዔ ላይ ተገልጿል። በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና መምህራን መካከል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ማነስ ምክንያት መግባባት እየተሳናቸው መምጣቱንና ይህም በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መምጣቱን ምሁራኑ በጥናታዊ ጽሁፋቸው አመላክተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ መምህር ፕሮፌሰር ዝናቡ ገብረማርያም ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ እንዳሉት ተማሪዎችና መምህራን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በደንብ ስለማይግባቡ የመማር ማስተማሩ ሂደት በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ አይደለም፡፡ ተማሪዎቹ ትምህርቱን በደንብ ሳይረዱት ይቀራሉ። ችግሩ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲዎች የዘለቀ ሲሆን የቋንቋው ክፍተት በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ላይ የተደቀነ ግንባር ቀደም አደጋ ነው።
ክፍተቱ ከተማሪዎቹ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመርቀው በሚወጡ መምህራን ላይም ይስተዋላል። በዚህም የተነሳ የአገርና የሕዝብ ሀብት እየባከነ መሆኑንና በዘርፉ የሚፈለገውን ግብ ለማሳካትም እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ፕሮፌሰር ዝናቡ አክለው ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ሎሬት ጥሩሰው ተፈራ በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መግባባት ችግር ሲሆን በአማርኛ መግባባት ይቻል እንደነበርና ፣አሁን ግን በሁለቱም ቋንቋዎች መግባባት የሚቸግርበት አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል።
ትምህርት የሚሰጥበትን ቋንቋ የማያውቅ ሰው የሚማረውን ሊረዳ፣ ምርምር ሊያደርግ፣ እውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ሕይወቱን ሊለውጥ አይችልም። ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችግር ስላለባቸው ተገቢውን ዕውቀት ለማስጨበጥ መቸገራቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ገልጸዋል።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ሳይንስ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ጸጋዬ በበኩላቸው ተማሪዎችና መምህራን ሃሳባቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ መግለጽ ይቸገራሉ። በዚህም የተነሳ የሚፈለገውን ዕውቀትና ክህሎት እንደማይጨብጡና ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል።
የቋንቋ ሥልጠና መስጠት፣ ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን መምህራንን መመልመል፣ በተከታታይ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ፣ የቋንቋ ክህሎትን ለማዳበር የሚረዱ መጻሕፍትን ማቅረብ፣ የግል ትምህርት ቤቶችን የቋንቋ ማስተማር ልምድ መውሰድ፣ የሌሎች አገራት ተሞክሮን በመቅሰም ለኢትዮጵያ በሚስማማ መልኩ ማዘጋጀት፣ ቤተሰብ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ መነጋገር፤ የተማሪዎችን ተነሳሽነት ለመጨመር የሚረዱ አሠራሮችን መተግበር የማስተማሪያ ቋንቋውን ወደ አገርኛ መቀየርም ሌላው መፍትሄ መሆኑን ዶክተር ሙሉጌታ በመፍትሄነት ጠቁመዋል።
ያልተደራጀውን የቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ በማስተካከል፣ የቋንቋ ቤተ ሙከራዎችን በመክፈት፣ የመምህራንን አሰለጣጠን በመቀየር እና ምልመላውን በውድድርና በብቃት በማድረግ የቋንቋ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ፕሮፌሰር ሎሬት ጥሩሰው አስገንዝበዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት አሰጣጥና ቋንቋን መሠረት በማድረግ ከአንደኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ባደረገው ጥናት 30 ሺ 605 ትምህርት ቤቶች ከዓለም አቀፍ መመዘኛ በታች መሆናቸውን ያመለክታል። ይህም በአገሪቱ ካሉ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች 89 በመቶውን ሲሸፍን፣ ከኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መካከል ዓለም አቀፍ መመዘኛ የሚያሟሉት 11 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጥናቱ አረጋግጧል።