በርካታ የታሰሩ ወጣቶችን የጫኑ 2 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አዘዞ ወታደራዊ ካምፕ ገቡ

በርካታ የታሰሩ ወጣቶችን የጫኑ 2 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አዘዞ ወታደራዊ ካምፕ ገቡ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ/ም) የአይን እማኞች ለኢሳት እንደገለጹት ዛሬ ከጠዋቱ 8 ሰአት ከ18 ደቂቃ ላይ በርካታ ወጣቶቹን የጫኑ 2 ኦራል መኪኖች ወደ አዘዞ ወታደራዊ ካምፕ ያመሩ ሲሆን፣ ወጣቶቹ በራሳቸው ልብስ አፋቸው ተለጉሞ፣ እጃቸውም በገደም ታስሮ የአይን እማኞች ገልጸዋል። ሁለቱም መኪኖች ስናይፐር በታጠቁ የአጋዚ ወታደሮች እየታጀቡ በመጓዛቸው ፎቶ ለማንሳት መቸገራቸውን የሚገልጹት የአይን እማኞች፣ በአዩት ነገር በእጅጉ መደናገጣቸውን ገልጸዋል። መኪኖቹ ከሰሜን አቅጣጫ ወደ አዘዞ መምጣታቸውን እንጅ ከየት አካባቢ እንደተነሱ እንደማያውቁ ገልጸዋል።
በቅርቡ በሮቢት አካባቢ ከጦር መሳሪያ ቅሚያ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ህዝብና በአጋዚ ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ ቆይቷል። እስረኞቹም ከዚሁ አካባቢ ሳይመጡ እንደማይቀር ይገመታል።