የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ መምህራን በወታደሩ ላይ የሰላ ትችት ሲያሰሙ አረፈዱ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ዛሬ በቅጽል ስማቸው ጄኔራል ሾማ እየተባሉ በሚጠሩ ወታደራዊ አዛዥ እና በፕ/ር ጨመዳ ፊኒኒሳ በተመራው የመመህራንና የሰራተኞች ስብሰባ ፣ ሰራተኞቹ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዝሩ ውለዋል። ከጠዋት 2 ሰአት እስከ 6 ሰዓት በቆዬው ስብሰባ ተሰብሳቢዎቹ በስሜት ይናገሩ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። አንድ መምህር፣ “ክቡር ጄኔራል፣ አሁን ልታስሩኝ ትችላላችሁ ነገር ግን በአለም ታሪክ ከህዝብ አብራክ የወጣ የመከላከያ ሰራዊት መልሶ የህዝብ ጠላት ሲሆን ያየሁት በኢትዮጵያ ነው፤ በግብጽ እንኳን ህዝብ ሲያምጽ ሰራዊቱ ከህዝብ ጎን ነው የቆመው፤ እኛ ጋ ግን ተቀራኒ ነው። ድንበር መጠበቅ ሲገባችሁ፣ የወጣችሁበትን ማህጸን እየጨፈጨፋችሁት ነው። በጣም አሳፈሪ ነገር ነው” ብለዋል።
ሌላ መመህር ደግሞ “ ቶሎ ሳይመሽ አሁኑኑ ከህዝብ ጋር ብትወግኑ መልካም ነው፤ ክቡር ጄኔራል፣ እርስዎ ዛሬ ከሁዋላዎ ያቆሙትን ጠባቂዎ ቢጨቁኑት ነገ አፈሙዙን ወደ እርስዎ ማዞሩ አይቀርም፣ አሁን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ነገር ይህ ነው፤ ህዝብ እየተጨቆነ ነው፣ በመንግስት ላይ ማመጹ ትክክል ነው፤ ከህዝብ ጎን መቆሙ ነው የሚያዋጣችሁ”ሲል ተሰብሳቢው ስሜቱን በከፍተኛ ጭብጨባ ገልጿል።
ሌሎች መምህራንና ሰራተኞችም እየተነሱ ተመሳሳይ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በተለይ የመከላከያ አዛዦች የራሳቸውን ካሜራ ይዘው መግባታቸውን ተከትሎ፣ ተሰብሳዎቹ “ ዛሬ በካሜራ ቀርጻችሁ፣ ነገ እርምጃ ልትወስድቡን ትችላላችሁ፣ እኛ ግን የሚመጣብንን ለመቀበል ዝግጁ ነን” ማለታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በስብሰባው ላይ ከተገኙት ወታደራዊ አዛዦች መካከል አንደኛው አዛዥ የተናገረው የብዙዎችን ስሜት መግዛቱ ታውቋል። እኔ ህዝብ እንደዚህ እንደሚጠላን እስከዛሬ አልገባኝም ነበር፤ ህዝብ ይወደናል፣ ህዝብ ከመከላከያ ጎን ነው የሚል እምነት ነበረኝ፤ ዛሬ ነው በህዝብ መጠላታችንን ያወቁትና የገባኝ” በማለት ስሜት የሚነካ ንግግር ተናግሯል። ስብሰባው የተለመደው የወታደራዊ እዙ ትዕዛዝ ተላልፎበት ተጠናቋል።
በሌላ በኩል የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ዛሬ ምዝገባ ቢያካሂዱም፣ ከፋሲካ በሁዋላ እንመለሳለን በማለት ግቢውን ለቀው ወደ የቤታቸው መሄዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል። ተማሪዎች ትምህርት መጀመር የሚገባቸው ከትናንት በስቲያ ነበር። የወታደራዊ እዙ ወኪሎች ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ ሲያስጠነቅቁ ቢቆዩም ተማሪዎቹ ግን ማስጠንቀቂያውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፤፡
ከምስራቅ ሃረርጌ ዜና ሳንወጣ፣ በዞኑ ውስጥ የሚካሄደውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ የመራሉ የተባሉ የቄሮ አባላት በሌሊት እየታደኑ እየተያዙ ነው። በተለይ የተቃውሞ ማእከል ነው በሚባለው በሸንኮር ወረዳ በርካታ ወጣቶች ታፍሰው ወደ ድሬደዋ ተወስደው ታስረዋል። የድሬዳዋ ዋናው አስር ቤትም በእስረኞች መጨነናቁ ታውቋል።
በርካታ ወጣቶች እስር በመፍራት ጫካ ውስጥ ለማደር መገደዳቸውን የአካባቢው ወኪላችን የላከው ዘገባ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩ ከተማም እንዲሁ በወጣቶች ላይ አፈሳ እየተካሄደ ነው። እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ የ11 ሰዎች ስም ዝርዝር የደረሰን ሲሆን፣ ወጣቶቹ ከኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል መታሰራቸው ታውቋል።
የእስር ዘመቻው የኦህዴድን የታች መዋቅር የማፍረስ እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ ተወስዷል።