የድል ሚድድ ደጋፊ ናቸው የተባሉ የኢትዮ-ሶማሊ ተወላጆች ቤተሰቦች አሁንም እየታሰሩ ነው

የድል ሚድድ ደጋፊ ናቸው የተባሉ የኢትዮ-ሶማሊ ተወላጆች ቤተሰቦች አሁንም እየታሰሩ ነው
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) የሶማሊውን ክልል መሪ የአቶ አብዲ ኢሌን አገዛዝ ለመቃወምና በክልሉ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን ለመታገል በውጭ የሚገኙ የሶማሊ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙትን ድል ሚድድ የተባለው ንቅናቄን ተከትሎ የንቅናቄው አባላትና አመራር ናቸው የተባሉ ቤተሰቦች እየተያዙ መታሰራቸው ቀጥሎአል።
በቅርቡ በክልሉ ዱል ሚድድ የሚል እና ህዝቡ ለመብቱ እንዲነሳ የሚጠይቅ ወረቀት መበተኑን ተከትሎ እንዲሁም በቅርቡ በስዊድን የሚካሄደውን ጉባኤ ተከትሎ ህጻናትን ሴቶች ሳይቀሩ መታሰራቸውን ከክልሉ የተላከልን መረጃ አመልክቷል።
የክልሉ ባለስልጣናት 150 የሚሆኑ ጂዳዋቅ የተባለውን ጎሳ አባላት የአገር ሽማግሌዎች በመጥራት ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ አስጠንቅቋል። ከዱል ሚድድ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም ሰው መኖሪያ ቤቱ እንደሚወስደበት ትእዛዝ ሰጥተዋል።
ስብሰባውን የመሩት የክልሉ የደህንነት ምክትል ሃላፊ አህመድ ዳሂር ፣ የቀድሞው የሶማሊ የደህነት ምክትል አዛዥ የነበረው ኮሌኔል ኢሮ፣ አሁን ሶማሊ ላንድ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የብሄራዊ ደህንነት ፍርድ ቤት ሃላፊ የነበረው ኮ/ል አብዱላከሪም ቃሊንሌ እንዲሁም ሶማሊ ክልልን ከኢትዮጵያ መገንጠን አለብን እንዲሁም ነፍጠኞችን ከክልሉ እናስወጣ የሚል አቋም እያራመደ የሚገኘው ሻለቃ አሊ አብዲ ኢሴ ናቸው።
አብዲ ኢሌ የቀድሞው የፓርላማ አባል የነበረውና በአሜሪካ የሚኖሩትን የሂርሲ ሞሃመድ ኔሮ፣ በጅጅጋ የንግድ ድርጅት ያላቸው እና ኖረዌይ የሚኖሩት አህመድ ሸይክ ባሽር ቤተሰቦች መኖርያና ንግድ ቤቶች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሰዎች ከቀብሪበያህና አራርሶ ቤታቸውን ተነጥቀዋል። አንዳንድ ተከራዮች ሳይቀሩ ቤታቸውን በ2 ሰዓት ውስጥ እንዲለቁ ካልሆነም እንደሚታሰሩ ማስፈራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ከአብዲ ኤሊ ጀርባ ሆነው የሶማሊ ክልልን እየመሩ ያሉት የህወሃት ጄኔራሎችና የቀድሞዋ ሶማሊያ መሪ የሲያድባሬ ባለስልጣናት መሆኑቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።