ታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የኢህአዴግ መንግሥት በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል በከሰሳቸው በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ 24 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትና ጋዜጠኞች ላይ 30ኛውን ምሥክር ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ አቀረበ፡፡
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ- ሕግ የድምጽ፣ የምሥል እና የሠነድ ማስረጃዎችን እንዲያቀርብ ለሃሙስ ከሰሃት ታህሳስ 12 ቀን 2004 ዓ.ም አዟል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ ለዐቃቤ- ሕግ ምሥክርነት ለመቅረብ ሳይፈቅድ በመቅረቱ ከማዕከላዊ መርማሪዎች ጋር እንደገና መናቆር ውስጥ ግብቷል ሲሉ ምንጮች አሳውቀዋል፡፡
የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ 30ኛ ምሥክር ሆነው የቀረቡት አቶ አለኸኝ ዳኘው ብሩ መርካቶ የተበላሹ ምጣዶችን የሚጠግኑ ኤሌክትሪሻን መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተው የመጣሁት በግንቦት 7 አመራር አባል በአቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ፣ በአቶ የሐንስ ተረፈ ወይም ጳውሎስ ላይ ለመመስከር ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ዐቃቤ- ሕግ በሚያነሳቸው መሪ ጥያቄዎች በመታገዝ ምስክሩ ጥር ወር 2003 ዓ.ም አበበ ታፈሰ (የዐቃቤ- ሕግ 28ተኛ ምሥክር) ደውሎ ጠራኝና የምነግርህ አለኝ ብሎኝ ፣ ዘለሌ ለግንቦት 7 አመራር ሁለት ሰው ለውትድርና ሁለት ሰው ደግሞ አውሮፓ ወጥቶ የሚማር 4 ሰው ይፈልጋልና ዝርዝሩን አስረዳኝ ብዬው አሳውቆኛል ብለዋል፡፡
በሌላ ጊዜ አቶ ዘለሌ ለአበበ ደውሎ ጳውሎስ የሚባል ሰው ይደውልልሃል ባለው መሰረት ደውሎለት ስድስት ኪሎ ተገናኝተው ስለገንዘቡ አታስብ እንዳለው አቶ አበበ ነግሮኛል፤ እኔም ወደ አውሮፓ ለመሄድ ተስማምቼ ስለነበር አቶ ዮሐንስ በሌላ ጊዜ ደውሎ ተገናኝተው ግንቦት 7 መመሪያና የጉዞ ካርታ በፍላሽ ዲስክ እንደሰጠው አቶ አበበ ነግሮኛል ሲለ ተናግረዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላም ሁለት ሰዎች በአስቸኳይ ተነሱ ተብሏል ብሎ የካቲት 18 ቀን 2003 ዓ.ም ማታ ነገረኝና እሁድ ጠዋት ወደ ጎንደር ጉዞ ጀመርን ባህር ዳር አድረን፣ በበነጋታው አቶ ዮሐንስ መጥቶ ለእያንዳንዳችን አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር (1500) ሰጥቶን ጉዞ ወደ ሱዳንና ወደ ኤርትራ አድርገናል ብሏል፡፡
ኤርትራ እንደደረስንም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የተባሉ የግንቦት 7 አመራር እና ኮሎኔል ፍጹም የተባለ የሻቢያ ወታደር አቀባበል አደረጉልንና አሪና በምትባል ተራራማ ቦታ ወሰደውን የግንቦት 7 ፖለቲካዊ ትምህርትና መመሪያ ደንብ፣ መሳሪያ መተኮስ፣ መገጣጠም፣ ፈንጂ አጠቃቀም፣ ኢንተርኔትና ኮምፒውተር አጠቃቀም አሰለጠኑን ሲሉ አክለዋል
ፍርድ ቤቱ “ዐቃቤ- ሕግ ምሥክሩን ወደ ዋናው የክስ ጭብጥ እንዲያመሩ እንዲያደርግ ያሳሰበ” ሲሆን፣ የተከላካይ ጠበቆችም “ዐቃቤ- ሕግ ሆን ብሎ ትላንት በምስክርነት ላይ እያሉ በጭንቀት ያለቀሱት 28ተኛው የዐቃቤ- ሕግ ምሥክር ያላስመዘገቡለትን ነጥቦች ሆን ብሎ ለ30ኛ ምስክር እንደተነገራቸው እያደረገ ማቅረቡ አግባብ አይደለም” ብለዋል፡፡
ምስክሩ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት- “ሥልጠናችንን እንደጨረስን አቶ አንዳርጋቸው ወደ ሱዳን ገንዘብ ተቀይሮ ዘጠኝ- ዘጠኝ መቶ ብር ሰጡንና ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳችሁ አንድ ሰው 4 ሰው እየቆጠረ እንዲያሰለጥንና በመንግሥት ባለሥልጣናትና ተቋማት ላይ ፍንዳታ እንድናደርስ” አዞናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች ባነሱት መስቀለኛ ጥያቄ ምስክሩ “ከአቶ ዮሐንስ ጋር ጎንደር ከገቡ በኋላ መገናኘታቸውንና ለግንቦት 7 የመለመሏቸውም አቶ አበበ ታፈሰ መሆናቸውን ተናግረዋል።”
ዐቃቤ- ሕግ የሰው ምሥክር ማጠናቀቁን በማስታወቁ ፣ ፍርድ ቤቱ የቪዲዮ ማስረጃዎችን ለመመልከት ታህሳስ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱን በትኗል፡፡
በሰሞኑ የፍርድ ቤት ድራማ በደንብ አልመሰከራችሁም በሚል አንዳንድ ግለሰቦች እየተዋከቡ መሆኑን ለኢሳት ተናግረዋል። ኢሳት የእነዚህን ሰዎች ድምጽ ቀርጾ ያስቀረ ሲሆን፣ ለጊዜው ለደህነታቸው ሲል ላለማውጣት ወስኖአል።
ይሁን እንጅ መስካሪዎች ይህን ተናገሩ፣ በእከሌ ላይ እንዲህ ብላችሁ መስክሩ ይህን ካላደረጋችሁ በህይወት አትኖሩም ተብሎ እንደተናገራቸው ኢሳት ያነጋገራቸው ምስክሮች ገልጠዋል።