ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች በአቶ መለስ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ብይን ተላለፈባቸው

11 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን   በሶማሌ ክልል ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው  የስዊድን ነዳጅ ፈላጊ ኩባንያ፤    እነሱ እንዳሉት ፦በአካባቢው ነዋሪዎችና በሰራተኞች ላይ  የሰብዓዊ መብት ጥሰት  መፈጸምና አለመፈፀሙን ለማጣራት” ፤ ከኦጋዴ ነፃ አውጭ ግንባር ተዋጊዎች ጋር በመሆን  ድንበር  አሳሰብረው  ወደ ክልሉ ለመግባት ሲሞክሩ በኢትዮጵያ ወታደሮች ቆስለው የተያዙት፤ ከስድስት ወር በፊት  ነው።

ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር በዋሉ ማግስት ሽብርተኝነትን ጨምሮ ተያያዥነት ያላቸው  ሌሎች ሁለት ክሶች የተመሰረተባቸው ቢሆንም፤ ጉዳያቸውን እየተመለከተ ያለው ፍርድ ቤት የሽብርተኝነት ክሱን ውድቅ በማድረግ ፦”ሽብርተኝነትን በመርዳት” እና “ ያለ ፈቃድ የአንድን ሉዓላዊ አገር ድንበር መጣስ” በሚሉት ሁለት ክሶች እንዲከላከሉ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።

ይሁንና በፍርድ ቤቱ የክርክር ሂደት ጋዜጠኞቹ  ላይ  ከቀረቡት ማስረጃዎች መካከል አብዛኞቹ   ጋዜጠኞቹ ለፖሊስ “ሰጥተዋቸዋል” ከተባለው ቃል ላይ የተወሰዱ  ቢሆኑም፤  ፖሊስ ካቀረባቸው ከነዚህ ማስረጃዎች ውስጥ አንዳቸውም እውነት እንዳልሆኑ ራሳቸው ጋዜጠኞቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

“ሽብርተኝነትና የሽብርተኛ ተባባሪ”  የሚለው ክስ እንደማይመለከታቸው የገለጹት ጋዜጠኞችም፤ ያለፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መግባታቸውን በማመን ይቅርታ መጠየቃቸውም አይዘነጋም።

ይሁንና  ከምርመራ ጋዜጠኝነት ሙያዊ ግዴታ አንፃር  ወደ ሌሎች አገሮችም በተመሳሳይ መንገድ መግባታቸውን የ አገሮቹን ስም በመጥቀስ ያብራሩት ጋዜጠኞቹ፤ ወደ ኢትዮጵያም የገቡትም ሙያዊ ግዳጃቸውን ለመወጣት እንጂ ለሌላ ተልዕኮ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ከዚህም ባሻገር ተከሳሾቹ ሽብርተኛም ሆነ የሽብርተኞች ተባባሪ ላለመሆናቸው፤ ከመቶ የሚበልጡ ጋዜጠኞች  ለመመስከር ዝግጁ መሆናቸውን ያሳወቁ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ግን በቂ ነው በማለት  የ20 ምስክሮችን ቃል ሰምቷል።

ሁሉም ጋዜጠኞች በሰጡት የምስክርነት ቃል የምርመራ ዘገባ( ኢንቨስቲጌቲቭ  ሪፖርት) በሚሰሩበት ጊዜ  ጋዜጠኞች  ከዚህም  በላይ ህይወታቸው አደጋ ላይ እስኪወድቅ ድረስ  ብዙ መስዋዕትነት በሚያስከፍሉ ስፍራዎች ላይ በመገኘት እንደሚዘግቡ በስፋት በማብራራት፤ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰንም  አሁን ላጋጠማቸው ፈተና የተዳረጉት  ለሙያቸው ካላቸው ፍቅር በመነሳት እንጂ  ሌላ ፍላጎትና ዓለማ ስላላቸው እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ቀጥታ ከላይ እንደወረደለት ሞትና ዕድሜ ልክ መፍረድ የለመደው በአቶ ሸምሱ ሲርጋጋ የሚመራው ፍርድ ቤት  ግን፤ ስለ ጋዜጠኞቹ ንፅህና ከበቂ በላይ ምስክሮችና ማስረጃዎች ቢቀርቡለትም፦ ጋዜጠኞቹ ከስዊድን ወደ ለንደን በመሄድ በኦጋዴ ነፃ አውጭ ግንባር መሪዎች የጉዞ አመቻችነት  በኬንያ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን በመጥቀስና፤  በምርመራ ዘገባ ስም  የአገርን ድንበር እንደጣሱና ከ አሸባሪ ድርጅት እንደተባበሩ በማውሳት     የአንድን ሉአላዊ አገር ድንበር በህገ ወጥ መንገድ  መጣስ እና የሽብርተኛ ድርጅት ተባባሪ በሚሉት ሁለት  ክሶች የጥፋተኝነት ብይን  አሳልፎባቸዋል።

አየር እንዳትተነፍሱ የሚል አንቀጽ ብቻ በቀረው በ ኢትዮጵያ  የሽብርተኝነት  ህግ  መሰረት ጋዜጠኞቹ  ከ 15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ እስራት ይጠብቃቸዋል።

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ፍሬድሪክ  ሬይንፌልድት   ጋዜጠኞቹ  ጥፋት ስለሌባቸው በነፃ ይሰናበታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው  መግለፃቸውን ተከትሎ-ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጉዳዩን አስመልክቶ  ባለፈው ሳምንት ለ ኢሳት በሰጡት አስተያዬት፤ ፍርድ ቤቱ በጋዜጠኞቹ ላይ ከቀረቡት ሶስት ክሶች ሁለቱን  ከመቀበሉ አኳያ በሚተላለፈው ብይን ላይ ተስፋ እንደሌላቸው መናገራቸው ይታወሳል።

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያና በስዊድን መካከል  ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ  በጋዜጠኞቹ ላይ በሚተላለፈው ብይን ላይ የራሱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የጠቆሙት የተቃዋሚ ፓርቲ  መሪው፤ ይህም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ይበልጥ ቫኢያበላሸው ይመጣል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በጋዜጠኞቹ ላይ የተላለፈውን የጥፋተኝነት ብይን ተከትሎ፤ ዓለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅቶች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።