የሰሜን ኮሪያዉ መሪ መሞትን ተከትሎ በዓለም ላይ በስልጣን ላይ ያሉ አምባገነን መሪዎች ቁጥራቸዉ ወደ 8 መዉረዱን ኢንተርኔሽናል ቢዝነስ ታይምስ ገለፀ

09 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ፤ ጠ/ሚር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በዓለም ላይ በስልጣን ላይ ያሉ አምባገነን መሪዎች ቁጥራቸዉ ወደ 8 መዉረዱን ኢንተርኔሽናል ቢዝነስ ታይምስ ገለፀ

ኢንተርኔሽናል ቢዝነስ ታይምስ የተባለዉ የመረጃ ምንጭ የሰሜን ኮሪያዉ ኪም ጆንግ 2ኛና የሊቢያዉ ሙአመር ጋዳፊ በ2011 በተወገደላት አለማችን ዉስጥ ቁጥራቸዉ ስምንት የሆኑ አምባገነኖች ዛሬም የመንግሰት ስልጣን ጨብጠዉ ሰብኣዊ መብቶችን በመርገጥና የፖለቲካ ጭቆና በማድረስ ላይ እንዳሉ አመልክቷል።

ኢንተርኔሽናል ቢዝነስ ታይምስ የመረጃ ምንጭ የኪም ጆንግ 2ኛን ከዚህ አለም በሞት መለየት በመግለፅ ባሰፈረዉ ፅሁፍ   በፈላጭ ቆራጭነት ህዝቦቻቸዉን እየረገጡ ከሚገዙት አምባገነኖች መካከል የሰሜን ኮሪያዉ ኪም ጆንግ 2ኛና የሊቢያዉ ሙአመር ጋዳፊ በ2011 በተወገደላት አለማችን ዉስጥ ቁጥራቸዉ ስምንት የሆነ አምባገነኖች ዛሬም የመንግሰት ስልጣን ጨብጠዉ ሰብኣዊ መብቶችን በመርገጥና የፖለቲካ ጭቆና በማድረስ ላይ እንዳሉ አመልክቷል። 

የ56 አመቱ የኢትዮጵያዉ ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ  ከኤርትራ ጋር በተደረገዉ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አላግባብ እንዲጨፈጨፉ ማድረጋቸዉ ተመልክቷል።

በተጨማሪ በ2005 በተደረገዉ የተጭበረበረ ምርጫ ምክንያት በፀጥታ ሃይሎቻቸዉ 193 ሰላማዊ ዜጎች እንዲገደሉ ማድረጋቸዉንና በኢትዮጵያና በሶማሊያ ዉስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀማቸዉ ለክስ መቅረብ እንደሚገባቸዉና ይህ ወንጀላቸዉ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በሚከታተለዉ የአለምአቀፍ ድርጅት ፕሬዝዳንት አማካይነት በ2011 የተመሰከረባቸዉ ግለሰብ መሆናቸዉን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ዘርዝሯል።

በተያያዘ ዜናም የሰሜን ኮሪያን ኮሙኒስታዊ ስርኣት ለረዢም አመታት የመሩትና “ የዘላለም ፕሬዝዳንት” ስም የተሰጣቸዉ ኪም ኢል ሱንግ እኤአ በ1994 ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ሰልጣኑን ሙሉ በሙሉ የወረሱት አምባገነኑ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ 2ኛ ፣ በ69 አመት እድሜያቸዉ በልብ ድካም በሽታ ህይወታቸዉ ማለፉን የአገሪቱ ቴሌቪዥን ገልጿል።

የአገራቸዉ ኢኮኖሚ እየተዳከመ በመሄድ ላይ ባለበትና በ1990ዎቹ በደረሰዉ የረሃብ አደጋ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቻቸዉ በረሃብ ሲያልቁ ወታደራዊ አቅማቸዉን ለመገንባት ቅድሚያ በመስጠት በዘረጉት ፖሊሲ በአለም አቀፍ ደረጃ ይወቀሱ የነበሩት የሰሜን ኮሪያዉ አምባገነን መሪ ለረዢም አመታት የልብና የስኳር በሽተኛ እንደነበሩ ይነገራል።

የኪም ጆንግ 2ኛ ሞት እንደተሰማ ደቡብ ኮሪያ ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ከማድረጓም በላይ የመንግስቱ ባለስልጣኖች ያላቸዉን የጉዞ እቅድ በሙሉ እንዲሰርዙ መመሪያ እንደሰጠች የደቡብ ኮሪያ የዜና አገልግሎት ዮን ሃፕ  ገልጿል።

 

የዜና አገልግሎቱ በተጨማሪ ከፕሬዝዳንቱ ሞት ዜና በማስከተል ሰሜን ኮሪያ የአጭር ርቀት ሚሳይል ወደ ምስራቅ የባህር ጠረፍ ዳርቻ መተኮሷን አስታዉቋል።

በኪም ጆንግ 2ኛ እግር የተተኩት የ27 አመቱ 3ኛ ታናሽ ልጃቸዉ ኪም ጆንግ ኡን ፣ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እንደሚመሩ  የተገለፀ ሲሆን ሟቹ ፕሬዝዳንትና መንግስታቸዉ ወጣቱን ለዚህ የስልጣን ዉርስ ሲያዘጋጁ እንደነበር ታዉቋል።

ባለፈዉ አመት ግንቦት ወር በቻይና ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ካደረጉ በሁዋላ ባለ አራት ኮከብ የወታደራዊ ጄኔራልነት ማእረግ የተሰጣቸዉና በአገሪቱ ፖለቲካ ዉስጥ የጎላ ሚና እንዲኖራቸዉ የተደረገዉ ወጣቱ ፕሬዝዳንት፣  ትምህርታቸዉን  በስዊዘርላንድ እንደተከታተሉና የእንግሊዝኛና የጀርመንኛ ቋንቋ እንደሚናገሩ ተገልጿል። 

ኪም ጆንግ ኡን እንደአባታቸዉ ሁሉ ከአለም ግዙፍ የሆነዉን ጦር በመያዝ አገራቸዉ በተያያዘችዉ አጨቃጫቂ የኑኩሌር ግንባታ ፕሮግራም እንደሚገፉበት ይጠበቃል። 

የሰሜን ኮሪያን የኢኮኖሚ ልማትና የፖለቲካ መረጋጋት ለማገዝ ቻይና የጎላ ሚና እንዳላት የሚታወቅ ሲሆን ለዚህም መሰረታዊዉ ምክንያት ሰሜኑ በሚገጥመዉ ቀዉስ ምክንያት በደቡብ ኮሪያ ሊዋጥ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ በቻይና ድንበር አካባቢ የአሜሪካን ጦር በገፍ ሊሰፍር ይችላል በሚል ስጋት እንደሆነ ይታወቃል። 

ላለፉት 31 አመታት ፍሪደም ሃዉስ የተባለዉ የአለም አገሮች ለሰብኣዊ መብትና ለዜጎች ነፃነት መከበር ከሚወስዷቸዉ እርምጃዎች በመነሳት በሚያወጣዉ አመታዊ የደረጃ ሰንጠረዥ  ሰሜን ኮሪያ በመጨረሻዉ ደረጃ ላይ ስትገኝ ፣ እኤአ በ2007 የአሜሪካን የሰብኣዊ መብት ኮሚቴ ቁጥራቸዉ 150 ሺህ የሚገመቱ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸዉ ምክንያት በእስር ላይ ሆነዉ የግዳጅ የጉልበት ስራ እያከናወኑ እንደነበር ገልጿል።