የህወሀት ጄኔራሎች እና የህወሀት ኩባንያ የሆነው ኢፈርት በፑንትላንድ እና ጁባ ላንድ ከፍተኛ ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው ተባለ

11 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:- የዛሬ 20 አመት ፣ የሲያድ ባሬ መንግስት እንደተገረሰሰ የሶማሊያ የጎሳ መሪዎች አገሪቱን ለብተና የዳረገ ጦርነት አካሄዱ፣ ጦርነቱም እስከ ዛሬ ቀጥሎ ህልቆ መሳፍርት ሶማሊያውያን ተገደሉ፣ ተሰደዱ።

ጦርነት ለአንዱ ሰርግ ይሆንለታል ለሌላው ደግሞ ተስካር ይሆንበታል እንደሚባለው፣ በሶማሊያ ጦርነት ከፍተኛ ትርፍ በማጋበስ ላይ የሚገኙ ጎረቤት አገሮች አሉ።

በ1940ዎቹ  አውሮፓ በጦርነት ትታመስ በነበረችበት ጊዜ፣ የአሜሪካ መንግስት የጦር መሳሪያዎችን ለአውሮፓ መንግስታት በመሸጥና ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ  በማበደር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ችሎ ነበር።

በቅርቡ ወደ ሶማሊያ በሰላም አስከባሪ ስም ጦራቸውን የላኩት  ኡጋንዳ ፣ብሩንዲ፣ ጅቡቲ ፣ እንዲሁም ጦራቸውን በሰላም አስከባሪ ስም ለመላክ ቃል የገቡት ፣ ነገር ግን ቀድም ብለው ጦራቸውን በራሳቸው ፈቃድ ሶማሊያ ያስገቡት ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ፣  ከአሜሪካ መንግስትና ከተባባሩት መንግስታት ድርጅት የሚለቀቀውን ገንዘብ ለመቀራመት አሰፍስፈው በመጠባበቅ ከጦርነቱ ትሩፋት ለማግኘት እየሞከሩ  ነው።

በሶማሊያ ጦርነት፣  ከኢትዮጵያ ይልቅ እየበለጸጉ የሚገኙት የህወሀት ጄኔራሎች እና የህወሀት ኩባንያዎች ናቸው ይላሉ የደህንነት ምንጮቻችን።

ራሳቸውን ነጻ የሶማሊያ ግዛት አድርገው የሰየሙት ፑንትላንድ እና ጁባ ላንድ የህወሀት ጄኔራሎችና ኢፈርት ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘርፉባቸው ግዛቶች ሆነዋል።

ታማን ምንጮች እንደሚሉት የህወሀት ጄኔራሎች ከኢትዮጵያ ህዝብ በተሰበሰበ ግብር የተገዙትንና የመከላከያ ሚኒስቴር ንብረት የሆኑትን የጦር መሳሪያዎች ለፑንትላንድ እና ለጁባ ላንድ የጦር መሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በመቸበቸብ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት በማጋበስ ላይ ናቸው።

የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ የሚከናወነው በካሽ ( ወይም በቀጥታ የእጅ ለእጅ ሽያጭ) በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከሽያጩ ስለሚገኘው ገንዘብ  እንደማያውቅ ምንጮች ይገልጣሉ።

ከሎጂስቲክስ አቅርቦት እስከ ጦር መሳሪያዎች ግምጃ ቤት ያሉት የሃላፊነት ቦታዎች በሙሉ በህወሀት አባላት የተያዙ በመሆናቸው ፣ የኦዲት ስራ ለመስራትና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ አስቻገሪ ሆኗል።

ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከአመት በፊት የመከላከያ ወጪ ኦዲት እንዲደረግ ሲጠየቁ “የትኛው ባለስልጣን ነው መከላከያን ኦዲት ሊያደርገው የሚችለው? በማለት መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ከአርቲስ እያሱ በርሄ ጋር በቅርበት ይሰራ የነበረ አንድ ባለሙያ፣ በመከላከያ ሰራዊት ስም ያለቀረጥ በርካታ እቃዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሲቸበቸቡ መታዘቡን ለኢሳት መግለጡ ይታወቃል።

የህወሀት ጄኔራሎች ለፑንትላንድ እና ለጁባ ላንድ የጦር አበጋዞች የሚሸጡዋቸው የጦር መሳሪያዎች በአብዛኛው ፣ በትከሻ ላይ የሚተኮሱ ላውንቸሮች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣  በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጥይቶች፣  የተለያዩ የእጅ ቦንቦች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ አንድ ክላሽንኮቭ እስከ 12 ሺ ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን፣ የህወሀት ባለስልጣናት ከሸጡዋቸው በሺዎች የሚቆጥሩ የጦር መሳሪያዎች በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንዳካበቱ መረጃዎች አመልክተዋል።

የህወሀት ጀኔራሎች በፑንትላንድ እና በጁባ ላንድ ከሚቸበችቡት የጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ፣ የህወሀት ኩባንያ የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ ደግሞ በጦርነቱ ጊዜ በእነዚህ አገሮች የወዳዳቁትን የጦር መሳሪያዎች እና የተለያዩ ብረታ ብረቶች በመሰብሰብ መቀሌ ወደ ሚገኘው ፋብሪካው እያጋዘ ነው።

መስፍን ኢንጂነሪንግ ከፈራረሱ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሀይል ማመንጫዎች ከወዳደቁ መኪኖች፣ ከባድ ጦር መሳሪዎች የተገኙትን የአርማታ ብረታብረቶች፣ እንዲሁም  የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን የህወሀት እህት ኩባንያ በሆነው ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ መኪኖች  እየጫነ በመውሰድ ላይ ነው።

መስፍን ኢንጂነሪንግ  ለፑንትላንድ እና ለጁባ ላንድ የጦር አለቆች ክፍያ ይፈጽም አይፈጽም  አልታወቀም።

ይሁን እንጅ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከዩክሬን እና ከቱርክ ያስመጣ የነበረውን የብረታ ብረት አቅርቦት በመቀነስ፣ ያለቀረጥ ከሁለቱ አገሮች እያስገባ ያለው ብረታ ብረት የተለያዩ ድጎማዎች የሚደረጉለትን ኩባንያ እጅግ ትርፋማ ሊያደርገው ይችላል ተብሎአል።

የህወሀት ባለስልጣናት በፑንትላንድ እና በሶማሊላንድ የጦር አበጋዞች መካከል ያለውን የድንበር ግጭት በመጠቀም፣ በፑንትላንድ ገዢዎች ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ይታወቃል።

የፑንትላንዱ መሪ አብዱረህማን ሙሀመድ ፋሩሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተመላልሰዋል።

በጁባ ላንድ ደግሞ የህወሀት ጄነራሎች ፣ በአንድ በኩል የጁባ ላንድን መመስረት እንደሚቃወሙ በማስመሰል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለጁባ ላንድ መሪዎች የጦር መሳሪያ በመሸጥ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማጋበስ ላይ ናቸው።

በወ/ሮ አዜብ የሚመራው የጫት ድርጅት ወደ ሶማሊላንድ ጫት በመላክ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያገኝ ይታወቃል።

በመከላከያ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና የአዛዥነት ቦታዎች የተቆጣጠሩት የህወሀት ጄኔራሎች መሆናቸውን ግንቦት7 ከሁለት አመት በፊት ባወጣው ዘገባ መግለጡ ይታወሳል።

አብዛኞቹ የህወሀት አባላትም ዘመናዊ ቤቶችን በቦሌ ክፍለ ከተማ እና በሌሎችም ዋና ዋና ከተሞች መስራታቸው ይታወቃል።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የተባለው ተቋም ከኢትዮጵያ በሙስና፣ በጉቦ፣ በድለላና በዋጋ ማስተካከያ ባለፉት 7 አመታት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ መውጣቱን ይፋ አድርጎ ነበር።

በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።