(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2010)
የፖለቲካ እስረኞች በምህረት ሳይሆን በይቅርታ ህጉ መሰረት ሊፈቱ እንደሚችሉ በፌደራሉ ዋና አቃቢ ህግ መገለጹ አፈጻጸሙን አጠራጣሪ ማድረጉን ታዛቢዎች ገለጹ።
ዋና አቃቢ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ከዚህ ቀደም እስረኞች በምህረት ይለቀቃሉ በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተገለጸውን በመቃረን መግለጫ ሰጥተዋል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት በአቶ ጌታቸው መግለጫ መሰረት እስረኞቹ ይቅርታ ካልጠየቁ ሊፈቱ የሚችሉበት ሁኔታም አይኖርም።
በኢትዮጵያ የእስረኞች አፈታት ህግ መሰረት ምህረትና ይቅርታ ልይነት አላቸው።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ግምገማን ተከትሎ ለፖለቲካና ዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት ሲባል እስረኞች በምህረት ሊፈቱ እንደሚችሉ አራቱ የኢሕአዴግ አመራሮች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተገልጾ ነበር።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች በሀገሪቱ ህግ መሰረት በምህረት ይፈታሉ ነበር ያሉት።
አቶ ሃይለማርያም ይህን ካሉ በኋላ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በእስረኞች አፈታት ጉዳይ ላይ ያወጣውን መግለጫ ከ6 ጊዜ በላይ በመሰረዝና በመደለዝ ለ7ኛ ጊዜ ያስተካከለው መግለጫ እንዲነበብ አድርጓል።
ታዛቢዎችና የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት የፖለቲካ እስረኞቹ በምህረት ቢለቀቁ ኖሮ በሕጉ መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከወህኒ ቤት ጓዛቸውን ጠቅልለው መውጣት ይችሉ ነበር።
አሁን ባለው ሁኔታና የፌደራሉ ዋና አቃቢ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በገለጹት መሰረት ግን እስረኞቹ የሚለቀቁት በምህረት ሳይሆን በይቅርታ ሕጉ ብቻ ነው።
ታዛቢዎችና የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት የፖለቲካ እስረኞቹ በይቅርታ ህጉ ብቻ የሚፈቱ ከሆነ ይቅርታቸውን በቅድሚያ ለማረሚያ ቤቱ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
በዚህ ሂደትም በአቃቢ ህግ በኩል ጉዳዩ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቀርቦ መፈቀድ ይኖርበታል ነው ያሉት።
አቶ ጌታቸው አምባዬም ይህን ሂደት ለማለፍ የ2 ወራት ጊዜ እንደሚፈጅ ፍንጭ ሰጥተዋል።
እስረኞቹ ከዚህ ቀደም እንደሆነው የፈጸምነው ስህተት የለም ይቅርታ አንጠይቅም ካሉም በዚያው በእስር ቤት ሊቀሩ እንደሚችሉም ታዛቢዎች ይናገራሉ።
የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ በይቅርታ የተፈታ ሰው ይቅርታው ተነስቶ ዳግም እስር ቤት ሊወረወርበት የሚችልበት እድል አለ።
ክሳቸው ተቋርጦ ይፈታሉ የተባሉት እስረኞችም አስፈላጊ ሲሆን አቃቢ ህግ ክሱን እንደገና ሊያንቀሳቅስ እንደሚችልም ነው የተገለጸው።