ህወሃት በክልሉና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያየ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2010)

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሃት በክልሉና በሀገራዊ ጉዳዮች እየተወያየ መሆኑን አስታወቀ።

ሀገሪቱን ስጋት ላይ የጣሉ አመራሮች ላይም ርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቋል።

የህወሀት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የትግራይ ህዝብ በአመራሮቹ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ተደርጓል ሲሉም በስም ያልጠቀሷቸውን አመራሮች ተጠያቂ አድርገዋል።

የህወሀት 7ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ከተጀመረ አንድ ሳምንቱን አጠናቋል።

ከመላው ዓለም የህወሃት ደጋፊዎችና አባላት የተወከሉበት፣ በሚዲያውና በማህበራዊ መድረኮች የድርጅቱን እንቅስቃሴና ዓላማ የሚያስተላልፉ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የተሳተፉበት፣ ከየወረዳው የድርጅቱ ተወካዮች የታደሙበት በአጠቃላይ ከ2500 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት እንደሆነ ተገልጿል።

ከአባልና አጋር ድርጅቶች መሪዎች በክብር እንግድነት ይገኛሉ የተባለ ሲሆን የኦሮሚያና የአማራ ክልላዊ ፕሬዝዳንቶች አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወደ መቀሌ እንዳልሄዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ያልተገኙበት ምክንያት ባይታወቅም በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት ዕልባት እንዳላገኘ አመላካች ነው ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

የህወሃት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅሶ የህወሃት ልሳን ሬዲዮ ፋና እንደገለጸው በ7ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ እየተመከረ ያለው ስለትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን ስለኢትዮጵያ አጠቃላይ ችግሮች ነው።

ክልላዊ ፓርቲ የሀገሪቱን ችግር በመንቀስ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥበት አሰራር ከፌደራል ስርዓቱ ጋር የሚጣረስ ነው የሚሉት ታዛቢዎች ህወሃት ሌሎቹን አባል ድርጅቶች በክልላቸው ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ብቸኛው የሀገሪቱ ወሳኔ ሰጪ አካል መሆኑን የቀጠለበት ጉባዔ ነው ሲሉም ገልጸውታል።

አቶ ጌታቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያ ላይ ስጋት የደቀኑ አመራሮችና አሰራሮች ላይ ለውጥ ይደረጋል።

የትግራይ ህዝብ በህወሃት አመራሮች ላይ ጥርጣሬና ስጋት እንዲያድርበት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው ይህን ያደርጉ አመራሮችም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

አቶ ጌታቸው በስም ባልጠቀሷቸው አመራሮችና አሰራሮች ላይ ለውጥ እንደሚኖርና ርምጃ እንደሚወሰድ መግለጻቸው በቀጥታ ኦህዴድና ብአዴን ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።

ህወሃት የማጽዳት ስራዬን አጠናቅቄያለሁ፣ ሌሎቻችሁም ተመሳሳይ ርምጃ መውሰድ አለባችሁ የሚል ግፊት እያደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በመሆኑም የአቶ ጌታቸው የዛሬ መግለጫ ላይ የአመራር ለውጥ ይኖራል ያሉት ሌሎቹን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን የሚመለከት ለመሆኑ ፍንጭ የሚሰጥ ነው ተብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሀት ካሰመረው ወሰን አልፈው፣ ከክልላቸው ጉዳዮች ተሻግረው ሀገራዊ አጀንዳዎችን በማንሳት መግለጫዎችን መስጠት የጀመሩት የኦህዴድና የብአዴን አመራሮች በህወሃት አዲስ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል ነው የአቶ ጌታቸው ረዳ መግለጫ የሚያመላክተው።

የትግራይ ህዝብ በህወሃት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ተደርጓል ያሉት አቶ ጌታቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ህወሀት በውስጡ በተፈጠረ ክፍፍል ወደስምምነት መድረስ ባለመቻሉ ጉባዔው ከታቀደለት ጊዜ በላይ ሊወስድ ይችላል።

የድርጅቱ ሚስጢሮችና የሊቀመንበሩ የወሲብ ቅሌት የሚያሳዩ መረጃዎች ለህዝብ መለቀቃቸው በአመራሮቹ መሃል ልዩነቱ እየሰፋ ለመምጣቱ አመላካች እንደሆነም የፖለቲካ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።