(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2010)
የአዲስ አበባ ወረዳዎች የብአዴን አመራር አባላት የአማራ ሕዝብ ሆድ ብሶታል በሕወሃት አገዛዝም ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ነው ሲሉ አማረሩ።
የብአዴን ካድሬዎች ያካሄዱት የጥልቅ ተሃድሶ የግምገማ ቃለጉባኤ ኢሳት እጅ ገብቷል።
ካድሬዎቹ የሕወሃት የበላይነት ስለመኖሩም ማረጋገጫ በማቅረብ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
የአዲስ አበባ ብአዴን ካድሬዎች ባካሄዱት ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ በየወረዳዎቻቸው የሚገኙ የሕወሃት አመራሮች ቁልፍ ቦታዎችን እንደተቆጣጠሩ ይፋ አድርገዋል።
የሕወሃት የበላይነት በየተቋማቱ ስለመኖሩ የተስማሙት የአዲስ አበባ ወረዳ ካድሬዎች በተለይ የመከላከያ ሰራዊት አመራር በትግራይ ተወላጆች መታጨቁን ነው የገለጹት።
ይህ ብቻ አይደለም በየትኞቹም ተቋማት ያሉ ቁልፍ ቦታዎች በነሱ የተያዙ ናቸውም ብለዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመቃብር አስነሺና የአይነስውር ማህበራት ሳይቀሩ የሚመሩት በሕወሃት ሰዎች መሆኑንም የግምገማ ሰነዱ ያመለክታል።
ጉምሩክ ላይ በየቦታው እነሱ ናቸው፣በትግርኛ ከተናገርክ ያሳልፍሃም ሌላው ግን ይወረሳል፣አዲስ አበባ ቦሌ ወረዳ 22 ገርጂ እንዲሁም የጀሞ አካባቢም የትግራይ ከተማ እስከመባልም ደርሷል ነው ያሉት።
በብዛት የሚነገረው ቋንቋ ትግርኛ ብቻ እስከ መሆን ደርሷልም ባይ ናቸው።
የብአዴን ካድሬዎች በአማራ ክልል ለሚነሱ ችግሮች ለምን ሽእቢያና አርበኞች ግንቦት 7ን እንደምክንያት እናነሳለን።ችግሩ ያለው በሕወሃትና በሕወሃት ብቻ ነው ሲሉም አማረዋል።
በርካታ ጉዳዮችን የያዘው የአዲስ አበባ ብአዴን ካድሬዎች የግምገማ ሰነድ እንደሚያመለክተው ሕወሃት በግዳጅ የወሰዳቸውን የአማራ መሬቶችን መመለስ ይኖርበታል የሚል ሃሳብም ተካቶበታል።
ይህም የወልቃይትና ጠገዴ ብቻ ሳይሆን የሰሜን ወሎ የነበሩ የራያ፣ቆቦ፣አላማጣና በጎንደርም እነ ሁመራ ተመላሽ መሆን እንዳለባቸው የብአዴን ካድሬዎቹ ጠይቀዋል።
ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ሁኔታም ትልቅ ጦስ ያለበት ነው ሲሉም አሳስበዋል።
ሲዳኖች የአማራ የእርሻ ቦታዎችን ይዘው ገደላማውን የእናነት ነው ማለታቸው አግባብ አይደለምም ብለዋል።
በብአዴኑ “ጥረትና” በሕወሃት “ኢፈርት” መካከል ስላለው ሰፊ ልዩነትም ካድሬዎቹ ተችተዋል።
ጋይንትና ግንደወይን የሚመረተው እንጨት ወደ መቀሌ ሄዶ ፋብሪካ ሲሆን ጥረት ግን እንጨትና ባህርዛፍ ቆርጭ ሆኗል ነው ያሉት።
ብአዴን ሕወሃትን ተጠራጥሯል የሚባለውም መስተካከል እንዳለበት ያሳሰቡት ካድሬዎቹ ይልቁንስ ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ናቸው ይላሉ።
ሕወሃቶች ሌላውን ስለሚጠራጠሩና ስለማያምኑ ትልልቅ የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማትን በእነሱ የጸጥታ ሃይሎች ብቻ ማስጠበቃቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
መጠራጠሩ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ካለ ብሄር የሚለው ጠፍቶ አንድ ኢትዮጵያ ብለን ሀገራችንን ብናለማ ይሻላል ሲሉም ነው የተናገሩት።
የብአዴን ካድሬዎቹ በግምገማቸው ኢሕአዴግ ራሱን ችሎ አንድ ፓርቲ ይሁን ሲሉም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባው የብአዴን ካድሬዎች የግምገማ ሰነድ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተከሰተው ብሔር ተኮር ግጭት የስርአቱ ውጤት ነው ሲሉም ድርጊቱን አውግዘዋል።