የሕወሃት አገዛዝ ከፍተኛ የእህል ክምችት ወደ ትግራይ እያስገባ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2010)

በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃውሞ የከፋ ደረጃ ይደርሳል በሚል የሕወሃት አገዛዝ ከፍተኛ የእህል ክምችት ወደ ትግራይ እንዲገባ እያደረገ መሆኑ ተነገረ።

መጪው ጊዜ ያስፈራው የህወሃት መንግስት ቀደም ሲልም ግዙፍ የእህል ጎተራ በማስገንባት እህል ሲያከማች መቆየቱ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ ተጨማሪ እህል ከአማራ አካባቢና ሌሎች የኢትዮጵያ አምራች አካባቢዎች ከአርሶ አደሩ በርካሽ ዋጋ እየገዛ ወደ ትግራይ እያጓጎዘ መሆኑ ታውቋል።

የትግራይ ክልል ብዙ እህል በማምረት የሚታወቅ አካባቢ አይደለም።

በኢትዮጵያ በሕወሐት አገዛዝ ዘመን ለበርካታ ጊዜ ድርቅ ሲያጋጥም ግን በአካባቢው የእሕል እጥረት የሚባል ነገር ተከስቶ አያውቅም።

ምክንያቱ ደግሞ የሕወሃት አገዛዝ ያለውን ስልጣንና አቅም መነሻ በማድረግ ከፍተኛ እህል ከአማራና ከተለያዩ የኢትዮጵያ አምራች አካባቢዎች እየገዛ ስለሚያከማች መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይናገራሉ።

ቀደም ሲል አምባሰል የሚባለው የብአዴን ድርጅት እህል ወደ ትግራይ በማጓጓዝ ተባባሪ ነበር።

እህሉን ከገበሬዎች በመግዛት በኩል ደግሞ መርከብ አምራቾች የስራ ማህበር የቅባት እህሎችን ጨምሮ ዋነኛ ተቋም ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።

የመርከብ አምራቾች የስራ ማህበር አመራሮች ከምስራቅ ጎጃም የትኖራና ብቸና እንዲሁም ከምዕራብ ጎጃም ቡሬና አቸፈር እንዲሁም ባህርዳር ትላልቅ መጋዘኖችን በማዘጋጀት እህል ገዝቶ ወደ ትግራይ ሲልክ ቆይቷል።

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስፈራው የሕወሃት አገዛዝ በደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም አማካኝነት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለነጋዲዎች ተሰጥቶ እህል እንዲገዛ ወስኗል።

የሕብረት ስራ ማህበራት እህልን በርካሽ ዋጋ ገዝተው በጉናና ትራንስ ትራንስፖርቶች አማካኝነት ወደ ትግራይ እንዲያጓጉዙ እቅድ ተይዟል።

ይህ ብቻ አይደለም በአማራ ክልል ከፍተኛ የባህር ዛፍ እንጨት ወደ ትግራይ እየተወሰደ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ባህር ዛፉንም በመርከብ አምራቾች ስራ ማህበር በኩል ሲያጓጉዝ መቆየቱ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ የአማራ አርሶ አደሮችን እህል በሕብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት በርካሽ ዋጋ እሕል ገዝተው በመጋዘን እያስቀመጡ መሆኑ ታውቋል።

ይህ በመጋዘን የተቀመጠ እሕልም ወደ ትግራይ ሲያጓጉዝ ሕዝቡ ተቃውሞውን በማሰማት በተሽከርካሪ ላይ የተጫነውን እህል ከጭነት አውርዶ እንዲከፋፈልና እንዲያስቀረው ጥሪ በመደረግ ላይ ነው።