የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ አወጣ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2010)

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሳምንት በፊት የጀመረው ስብሰባ አለመጠናቀቁን በማስመልከት ግንባሩ መግለጫ አወጣ።

በአባል ድርጅቶች ውስጥ አለመተማመንና መጠራጠር እንደነበርም መግለጫው ዘርዝሯል።

አዘቅት ውስጥም ገብተናል ሲልም ያክላል።

በአጠቃላይ ጉዳይ የተጀመረውና የቀድሞ አመራሮችን ያሳተፈው ግምገማ አሁንም መቀጠሉን በፓርቲና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለቀቀው የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ያስረዳል።

“እስካሁን በተደረገው ጥልቅ ግምገማ ከስኬት ጎዳና እያራቁን የሚገኙት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መታጣት፣ የእርስ በርስ መጠራጠር፣ የውስጥ ድርጅት ዲሞክራሲ እጦት፣ የህዝባዊ ወገንተኝነት መሸርሸር” መሆናቸውን የሚገልጸውና ረቡዕ ታህሳስ 11/2010 የወጣው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ተገቢ ውይይት ተደርጎባቸው የህዝብን የልማትና የሰላም ጥያቄ ለመመለስ መግባባት ላይ ተደርሷል ሲል ይገልጻል።

በፓርቲዎቹ መካከል የነበረው መጠራጠርና ሽኩቻ ምን እንዲሆንና ምንን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ግን ሳይገልጽ አልፎታል።

በዚህ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የትግራይ የበላይነትን የተመለከቱና ሌሎች አወዛጋቢ አጀንዳዎች የተነሱ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የኦህዴድና የብአዴንን አመራር ሕወሃት ለቀጠለው ግጭት ምክንያት ናችሁ በሚል ያቀረበው የውይይት ሰነድም ስብሰባውን በውጥረት እንዲሞላ ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀሱ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

የቀድሞው የኦህዴድ ሊ/መንበርና በቅርቡ በፈቃዳቸው የለቀቁት አቶ አባዱላ ገመዳ በመንግስት መዋቅርም ውስጥ ሆነ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የትግራይ የበላይነት ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ምክንያት እንደሆናቸው በዚህ ስብሰባ ላይ መናገራቸውም ይፋ ሆኗል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች የተፈለገውን ውጤት ባለማምጣታቸው ወደ አዘቅት እየተመለስን ነው የሚለው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ፣ በሃገሪቱ ለተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት በዋነኛነት በድርጅቱ አመራሮች ደካማነት የተከሰተ እንደሆነ መገምገሙንም አስታውቋል።

በቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የኢህ አዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ታህሳስ 11/2010 የተጀመረ ቢሆንም ከሳምንት በላይ ሳይጠናቀቅ አሁንም መቀጠሉን የድርጅቱ መግለጫ አስታውቋል።

የሕውሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአራት ቀናት የጠራው ስብሰባ ከወር በላይ መቀጠሉን ተከትሎ ከሶስት የማረጋጊያ መግለጫ በኋላ አቶ አባይ ወልዱና ወ/ሮ አዜብን ከስራ አስፈጻሚ አባልነት በማስወገድ መጠናቀቁ ይታወሳል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ምን ያህል ግዜ እንደሚወስድና በነማን ላይ ርምጃ ወስዶ እንደሚጠናቀቅ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።