(ኢሳት ዜና–መስከረም 17/2010) ከባሌ ዞን ለተፈናቀሉ ከሶስት ሺ በላይ የሲዳማ ተወላጆች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ።
በህወሃት መንግስት የእጅ አዙር ትዕዛዝና ግፊት በኦህዴድ አስፈጻሚነት በታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለው ማፈናቀል ሕጻናትን ጨምሮ ነፍሰጡር እናቶችና ደካማ የሆኑ አዛውንቶች ከፍተኛ ጉዳት ላይ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ወገናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ የጠየቀው የሲዳማ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት የተፈናቀሉት የሲዳማ ብሔር ተወላጆችን ቀይ መስቀል ለጊዜው እየረዳቸው መሆኑ ታውቋል።
መፈናቀሉ የተከሰተው ከ15ቀናት በፊት ቢሆንም ትኩረት ሳያገኝ በመቅረቱ ችግሩ አሳሳቢ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል።
ከባሌ ዞን አንጌቶ ወረዳ የተፈናቀሉት 1700 አባዎራዎችን ጨምሮ 3200 የሲዳማ ተወላጆች ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ የገለጸው የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በክልላዊ መንግስቱና በፌደራሉም ጭምር የተደረገ ድጋፍ ባለመኖሩ ወገኖቻችን አደጋ ላይ ወድቀዋል ሲል አስታውቋል።
የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ በቀለ ወዮ መፈናቀሉ ከመፈጸሙ በፊት ግድያ እንደነበረ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ የውጭ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ነጌሶ ኦዳ እንደሚሉት ከ3ሺህ በላይ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች ከባሌ ዞን እንዲፈናቀሉ የተደረገበት ምክንያት በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ህዝቦችን ለማጋጨት የያዘው ፕሮጀክት አካል ነው።
የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ወዮም በተፈጠረው መፈናቀል ተጠያቂ የሚያደርጉት በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ነው።
አበጣብጠው ህዝብን ከህዝብ አጋጭተው በስልጣን የመቆየት ፖሊሲያቸውን ህዝቡ መንቃት አለበት ይላሉም።
የተፈናቀሉት ከ3ሺህ በላይ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ነጌሶ ኦዳ ኢትዮጵያውያን በፈለጉበት በመረጡበት ቦታ የመኖር መብታቸው ሊከበር ይገባዋል ሲሉም ይገልጻሉ።
ከምንም በላይ ስርዓቱ የበተነውነው የማጋጨት ሴራ ማክሸፍ ከህዝባችን ይጠበቃል ይላሉ አቶ ነጌሶ።
የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበርም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን የሲዳማ ብሄር ተወላጅ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡ ጥሪ ካደረጉ በኋላ ድርጊቱን ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።