የደመራና የመስቀል በአል በድምቀት ተከበረ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 17/2010) በኢትዮጵያና በመላው አለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ምዕመናኑ የደመራን በአል በድምቀት አከበሩ።

የመስቀልም በአልም በመላው ኢትዮጵያ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ ውሏል።

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በከፍተኛ ድምቀት የተከበረው የደመራ በአል ከኢትዮጵያ ውጪ በሰሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በተመሳሳይ ብዙ ምዕመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

ከአሜሪካ ርዕሰ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ በተጨማሪ በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ሎስአንጀለስ፣ አትላንታ፣ ሲያትል፣ዴንቨርና በሌሎች ከተሞችም በአሉ መከበሩ ታውቋል።

በአውሮፓ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮችም በአሉን ያከበሩ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ በእስራኤልም በአሉ መከበሩን መረዳት ተችሏል።

በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ በዱባይና አቡዳቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ የደመራ በአልን በድምቀት ማክበራቸው ታውቋል።

በባህሬን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የደመራን በአል አክብረዋል።

በአዲስ አበባ በተከበረው የመስቀል በአል ፓትሪያርኩ አቡነ ማትያስና የሕንዱ ፓትሪያርክ በእንግድነት በተገኙበት በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል።

በጎንደርና በደሴ በተከበረው የመስቀል በአል ምዕመናንና ቀሳውስት ምልክት የሌለበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዘው በመውጣት ስነ ስርአቱን በድምቀት ማካሄዳቸው ታውቋል።

በትግራይ መቀሌ የደመራ በአል ሲከበር ደመራውን ኮከብ የሌለበት ባንዲራ አልብሳችኋል በሚል የበአሉ ታዳሚዎች መደብደባቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የደመራ በአል በጎረቤት ሀገር ኤርትራ የአለም አብያተክርስቲያናት በተገኙበት በድምቀት መከበሩ ታውቋል።

የመስቀል በአል በኦሬንታል ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታዮች በብቸኝነት የሚከበረው በኢትዮጵያና በኤርትራ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

የደመራ በአል በአለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የተመዘገበ መሆኑም ይታወቃል።