(ኢሳት ዜና–መስከረም 16/2010) የሰብአዊ መብት ጠበቃና የሕግ ባለሙያ የትነበርሽ ንጉሴ የስዊዲን አማራጭ የኖቤል ሽልማትን ተቀዳጀች።
ራይት ላይቭሊሁድ አዋርድ የተባለውን ሽልማት ያገኘችው የትነበርሽ ንጉሴ ከሁለት ሌሎች የአማራጭ ኖቬል አሸናፊዎች ጋር 374 ሺህ ዶላር ገንዘብ ትካፈላለች።
የትነበርሽ ንጉሴ ሽልማቱን ያገኘችው ከ5 አመት የልጅነት እድሜዋ ጀምሮ ሊከላከሉት በሚችሉት በሽታ ምክንያት አይነ ስውር ብትሆንም በጥረቷ ስኬታማና ሌሎችንም የአካል ጉዳተኞች በመረዳት ላበረከተችው አስተዋጽኦ ነው።
ገና በ5 አመቷ በትኩሳት ህመም ትያዛለች።ትኩሳቷ እየጸና ቢሄድም ወደ ሆስፒታል የወሰዳት ግን አልነበረም።
በባህላዊ መድሃኒትና በጸበል ለመፈወስ ብቻ የተሞከረው በሽታ ሊድን አልቻለም።
ጭራሽ በሽታዋ ተባብሶ ለአይነ ስውርነት ዳረጋት።የትነበርሽ ንጉሴ ትኩሳቷ ብሶ አይኗን ለማጣት ብትዳረግም ህመሟና ጉዳቷ ሳያንስ የተረገመች ስለሆነች ጉዳቱ እንደመጣባት ተደርጎ በአካባቢው ማህበረሰብ ተፈረጀች።
የትነበርሽ እንደምትለው የህመሟ ምክንያት የማጅራት ገትር በሽታ ነበር።በሕክምና ሊከላከሉት እየተቻለ ለአይነ ስውርነት የዳረጋት በሽታ።
ርጉም ተደርጋ በመቆጠሯ ሞታ ባረፈችው ያላትም ብዙ ነበር።ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በአዲስ አበባ ሴት አካል ጉዳተኞችን በሚቀበለው አንድ የካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት ስትገባ የየትነበርሽ ንጉሴ ሕይወት መለወጥ ጀመረ።
ትምህርት አይነስውርነቴን ወደ እድል ቀይሮታል ትላለች።የትነበርሽ ንጉሴ በአሁኑ ጊዜ ታዋቂ የሰብአዊ መብት ጠበቃና የሕግ ባለሙያ ሆና ሕይወትን ድል አድርጋታለች።
ይህ ብቻ አይደለም ልክ በ35 አመቷ የስውዲን አማራጭ ኖቤል ሽልማትን በመቀዳጀት የድል ማማ ላይ መውጣቷን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
የትነበርሽ ከአንዲት ሕንዳዊት የህግ ባለሙያና ከሌላ ሴት ጋዜጠኛ ጋር የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማትን በማሸነፍ የ374 ሺህ ዶላር አሸናፊ ሆናለች።
ዛሬ በስዊዲን ርዕሰ ከተማ ስቶክሆልም ሽልማቷን የምትቀበለው የትነበርሽ ንጉሴ ማንም ቢሆን ማን በአካል ጉዳት ምክንያት ማንንም ዝቅ እንዳያደርግ ብላለች።
የትነበርሽ ላይት ፎር ዘወርልድ በተባለና በታዳጊ ሀገራት በአካል ጉዳተኞች መብት ላይ በሚሰራ ተቋም ውስጥ በከፍተኛ አማካሪነት ትሰራለች።
የትነበርሽ አይኔን በማጣት አንድ የአካል ጉዳት ቢኖርብኝም 99ኝ አይነት ግን ችሎታ አለኝ ስትል ስለራሷ በኩራት ትናገራለች።