ባለስልጣናት ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ መጣሉ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 9/2009)የቀድሞው የሕወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ በስልጣንና በጡረታ ላይ በሚገኙ የተወሰኑ ባለስልጣናት ላይ ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ መጣሉን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
ከባለስልጣናቱ ጋር ቅርበት ያላቸው ወገኖችም ሊወጡ ሲሉ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው መመለሳቸውንም ምንጮቹ አመልክተዋል።
የእስር እርምጃውን እየወሰደ ያለው ቡድን የፍርድ ቤት ትእዛዝ በማውጣት የጣለው ግልጽ አገዳና በመምሪያ የተላለፈ ማስጠንቀቂያ ባይኖርም ከሐገር ለመውጣት የተከለከሉ መኖራቸውን ግን የኢሳት ምንጮች አረጋግጠዋል።
ግልጽ ክትትል የሚደረግባቸው ባለስልጣናት መኖራቸውም የታወቀ ሲሆን ይህ ክትትል የቀድሞ ባለስልጣናትን እንዲጭምርም መደረጉ ታውቋል።
በዚህ ረገድ የውጭ ሀገር ጉዞ አስቀድሞ ያቀደና በድንገት የተዘጋጀ ባለስልጣናት ጭምር በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት ከሀገር እንዳይወጡ ተደርገዋል።
ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የተመለሰ ባለስልጣን ባይመዘገብም የቅርብ ዘመዶቻቸውና ሌሎች የንግድ ሰዎች ከአውሮፕላን ማረፊያው ብቻ ሳይሆን ከተሳፈሩበት አውሮፕላን ውስጥ ጭምርም እንዲመለሱ መደረጉን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ከፍተኛ ባለስልጣናቱ ለጉዞ ከመነሳታቸው በፊት አስቀድሞ በስልክ መመሪያ ስለሚሰጣቸው ቦሌ ላይ ሳይደርሱ ጉዟቸውን ይገታሉ ይላል መረጃው።
ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተመለሱት ውስጥ የታሰሩት ጥቂቶች ሲሆኑ ሌሎቹን ለግዜው ከሀገር መውጣት አትችሉም በሚል ወደ ቤታቸው እንደሚመልሷቸው መረዳት ተችሏል።
በተለይ ገንዛባቸው እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ከተጣለባቸው አምስት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ምርመራው በከፍተኛ ደረጃ በመቀጠሉ ከነዚህ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ባለስልጣናት በግልጽ ከሀገር እንዳይወጡ የቃል ትእዛዝ እንደተሰጣቸውም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በዝቅተኛ እርከን ላይ በሚገኙ ኢንጂነሮች ጥቂት የአክሲዮን ድርሻና በዋናነት በዶክተር አርከበ እቁባይ ቤተሰብ ከፍተኛ ድርሻ ከተቋቋመው አሰር ኮንስትራክሽን ጋር በተያያዘ የቀጠለው ምርመራ በአቶ አርከበ እቁባይና በዙሪያቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
በገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ድርጅትና ኢሊሊ ሆቴል ላይ የተጣለው የፍርድ ቤት እገዳ በነባር የኦህዴድ አመራሮች በተለይም በአቶ ሶፊያን አህመድና በአቶ አባዱላ ገመዳ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም አሳሪው ክፍል አቶ አባዱላ ገመዳ ላይ ትኩረት ስለማድረጉ የሚያሳዩ መረጃዎች አልተገኙም።
አቶ ሶፊያን አህመድን በተመለከተ ግን ዊንድሶር ካናዳ እስከሚገኘው ወንድማቸው አቶ መሀመድ አደም ድረስ የዘለቀ የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ተነግረዋል።
ሌላው እገዳ የተጣለበት ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን ንብረትነቱ የአቶ ዳንኤል ማሞ ሲሆን ይህ ድርጅት ከጅማ አስፋልት መንገድ ስራ እንዲሁም ከለገሀሩ ማሪታይም ህንጻ ብሎም በደቡብ ክልል ከሰራቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑ ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከኩባንያው ጋር ባላቸው ግንኙነት ዙሪያም ምርመራው መቀጠሉ ተመልክቷል።
ሆኖም ርምጃውን የሚወስደው ክፍል ለአቶ ሃይለማርያም ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ ርምጃ የመውሰድ ፍላጎት እንደሌለው ግን ምንጮች ገልጸዋል።
የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን ድርጅት በ5ኝነት ሀብቱ እንዳይንቀሳቀስ የታገደበት ድርጅት ሲሆን ይህ ኩባንያ ከስኳር ኮርፖሬሽኖች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሀብት የሰበሰበ እንደሆነም ተመልክቷል።
የንብረትነቱም ድርሻ ከአቶ የማነ ግርማይ ይልቅ የአቶ አባይ ጸሀዬ ይበልጣል የሚባለው ይህ ኩባንያ ላይም የተጀመረው ምርመራ ቢቀጥልም እስራቱ ወደ ላይ ሳይወጣ ስርስሩ ላይ ተገድቧል።
በሌብነት ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች ቁጥር 56 በደረሰበት በአሁኑ ወቅት በሚኒስትር ደረጃ የተጠየቀ ወይንም የታሰረ እንደሌለ ይታወቃል።
ከፍተኛው ባለስልጣን እስረኛ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ወይንም ተቀዳሚ ምክትል ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ጉጁ ብቻ ሲሆኑ ሌሎቹ ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም ዳይሬክተሮችና በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች መሆናቸው ይታወቃል።