ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት ሊዘጋ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 9/2009) አንጋፋውና ነባሩ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት ሊዘጋ መሆኑን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ገለጹ።
ዋና ስራ አስኪያጁ ኢንጂነር አካሉ ገብረህይወት እንደገለጹት ፋብሪካው ካለው አቅም ከግማሽ በታች እያመረተ ነው።
የሀገሪቱን የሲሚንቶ አቅርቦት የተቆጣጠረው ሞሶቦ ሲሚንቶ ከአቅሙ በላይ እያመረተ ሙገር ሲሚንቶ ሊዘጋ መቃረቡ ሆን ተብሎ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ።
የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ቀደም ባሉ አመታት የሀገሪቱን የሲሚንቶ ፍላጎት በመሸፈን ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ነበር።
ድርጅቱ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ጠንካራ የሰራተኛ ማህበርና በአገልግሎቱ ተጠቃሽ ተቋም ሆኖ ሲወደስም ቆይቷል።
በሕወሃት ኢህአዴግ የሚመራው አገዛዝ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን ፋብሪካውን የማዳከም ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
ሕወሃት ወደ ስልጣን ሲመጣ በአቶ ስዩም መስፍን ቦርድ ሰብሳቢነት ሲመራ በወቅቱ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ የነበሩትን ኢንጂነር ግዛውን ጨምሮ ኢንጂነር ባሶ አሰፋና ኢንጂነር መስፍን አቢ ለ3 አመታት በሙስና ስም ታስረው በኋላ ላይ በነጻ መለቀቃቸው ይታወሳል።
ሙገርን በማዳከም በመቀሌ የተገነባው ሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግን በየእለቱ ኣያደገና ምርቱም እየጨመረ እንዲመጣ ነው የተደረገው።
በሞሶቦ ሲሚንቶ ምርት ብቻ ከ23 በላይ በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች መገንባታቸው ይታወቃል።
ሞሶቦ በአሁኑ ጊዜ 2 ሚሊየን 1መቶ ሺ ቶን በአመት ሲያመርት ሙገር ግን ከ8 መቶ እስከ 9 መቶ ሺ ቶን በማምረት ከግማሽ በታች በሆነ አቅም ላይ ይገኛል።
ሙገር በተለያየ ጊዜ የማስፋፊያ ስራዎች ተከናውነውለታል ሲባል ቢቆይም በአሁኑ ጊዜ ግን ምርቱን ሙሉ ለሙሉ አቁሞ ሊዘጋ እንደሚችል የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አካሉ ገብረህይወት አስታውቀዋል።
ስራ አስኪያጁ እንደገለጹት ሙገር ፋብሪካ በአሁኑ ጊዜ ካለው አቅሙ ከግማሽ በታች ብቻ እያመረተ ይገኛል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኤሌክትሪክ ሃይል ማጣትና መቆራረጥ መሆኑን ገልጸዋል።እናም በየአመቱ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ኪሳራ እየደረሰ ይገኛል ነው ያሉት።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገላጻ የፋብሪካው ሲሚንቶ መፍጫና ማሸጊያ ማሽኖች በኤሌክትሪክ እጦት ምክንያት በአቅማቸው መንቀሳቀስ አልቻሉም።
የሙገር ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ በድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ አማካኝነት ያለውን ችግር ለፓርላማው ቢያሳውቁም መፍትሄ አልተገኘም ብለዋል።
እናም የሚመለከታቸው አካላት ሙገር ሲሚንቶን ከመዘጋት እንዲያድኑት ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ሃላፊዎችን ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻል ዘግቧል።