አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ ፈቀደ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 9/2009) አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ መፍቀዱን አስታወቀ።
ይህም የሀገሪቱን ብድር ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ እንዳደረሰው ተመልክቷል።
በዜሮ ወለድ ለድሃ ሀገራት የሚሰጠው ይህ ብድር በቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት እንደሚለቀቅም ተመልክቷል።
የሕወሃት ኢህአዴግ መንግስት በአንድ አመት በብድር የሚያገኘው ገንዘብ የደርግ መንግስት በ17 አመት ከተበደረው ብልጫ እንዳለው መረጃዎች አመልክተዋል።
በአለም ባንክ ስር ያለው አለም አቀፉ የልማት ማህበር/አይ ዲ ኤ/ለመጪው የፈረንጆቹ አመት ለኢትዮጵያ የመደበው የብድር መጠን 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ሲሆን በእለቱ ምንዛሪም 107 ቢሊየን 456 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር ያህል ነው።
ገንዘቡ ለውሃ አቅርቦት፣ለንጽህና አጠባበቅ፣ለትምህርትና ለንግዱ ዘርፍ እንዲሁም ለሎጅስቲክና ለልማት በተጨማሪም ለሴቶች የስራ ፈጣሪነት ላይ ቅድሚያ እንደሚሰጥም ተመልክቷል።
ብድሩን የሰጠው በአለም ባንክ ስር የሚገኘው አለም አቀፉ የልማት ማህበር የዛሬ 60 አመት አካባቢ የተመሰረተና የአለም ድሃ ሀገራትን የሚደግፍ ተቋም እንደሆነም ተመልክቷል።
በአለም ላይ የሚገኙና ድሃ የሚባሉ 77 ሀገራትን የሚደግፈው ይህ ተቋም ድሃ ብሎ ካስቀመጣቸው ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ 39ኙ የሚገኙት በአፍሪካ ነው።
ይህ ተቋም ከሁለት አመት በፊት በተመሳሳይ የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ የሰጠ ሲሆን፣ የአምናው ብድር 900 ሚሊየን ዶላር ነበር።
እየተገባደደ ባለው የአውሮፓውያኑ 2017 አለም አቀፉ የልማት ማህበር ለኢትዮጵያ የሰጠው የብድር ድጋፍ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ነበር።
ለቀጣዩ አመት 2018 ተቋሙ ቃል የገባውን 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላርን ሳይጨምር እስካሁን የሰጠው ብድር 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ሲሆን በአጠቃላይ ከማህበሩ የተገኘው ብድር 12 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
ከሌሎች እርዳታ ለጋሾችና አበዳሪዎች የተገኘውን ሳይጨምር ከዚሁ አለም አቀፍ ተቋም የተገኘው ብድር ብቻ ሁለት የአባይ ግድብን ወይንም የህዳሴውን ግድብ ገንብቶ ግልገል ጊቤ ሶስትን እንደሚጨምር መረዳት ተችሏል፡፡
ባለፉት 26 አመታት ከአለም አቀፉ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ተቋም /ኦ ኢ ሲ ዲ/ የተገኘው እርዳታ ብቻ ወደ 50 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን ከልዩ ልዩ አበዳሪ ተቋማትና መንግስታት በተመሳሳይ የተሰጠው ብድር ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑ በራሱ በመንግስት በይፋ ታምኖበታል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንደተመለከተው ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የተሰጠውን ብድር ሳይጨምር የሀገሪቱ እዳ 23 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የተሰጠውን ሲጨምር የእዳው መጠን ምን ያህል እንደሆነግን አልተገለጸም።
የኢህአዴግ መንግስት በአንድ አመት ውስጥ በእርዳታ ብቻ የሚያገኘው ገንዘብ የቀድሞው የደርግ መንግስት በስልጣን ዘመኑ ለ17 አመታት ከተሰጠው ብድር እንደሚበልጥም ታውቋል።
የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በፈጠረው አለም አቀፋዊ ምቹ ሁኔታ እርዳታና ብድር በከፍተኛ ደረጃ የሚያገኘው የሕወሃት/ኢሕአዴግ/ መንግስት የዜጎቹን ሕይወት መለወጥ አለመቻሉና ችጋር መበርታቱ አነጋጋሪ ሆኗል።