ሐምሌ ፫ ( ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከጅቡቲ ወደ መቀሌ በሚዘረጋው የባቡር መስመር እርሻ ቦታቸውን የተነጠቁ አርሶ አደሮች “ተገቢውን የመሬት ካሳ እንከፍላችኋለን” ቢባሉም ለሶስት አመታት ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያ ባለማግኘታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ገለጹ፡፡
በአማራ ክልል ቆቦ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች በተለይ ለሪፖርተራችን እንደገለጹት፤ከመቀሌ እስከ ትግራይ ድንበር ድረስ ለሚገኘው አካባቢ ደረቅ መሬት በማለት የመሬት ካሳ ክፍያውን ከከፈሉ በኋላ ወደ አማራ ክልል ሲገቡ “የመስኖ መሬት በመሆኑ በልዩ ጥናት ክፍያው ይዘጋጃል” በማለት የተሻለ ክፍያ እንደሚኖር ቢነገራቸውም ፣ ከግንቦት ወር 2007 ዓም. ጀምሮ መሬታቸውን ተነጥቀው ምንም ዓይነት ካሳ አለማግኘታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ለችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ከአስራ አምስት ሄክታር በላይ የመስኖ ቦታ እንደተወሰደባቸው የተናገሩት አርሶ አደር፣ በመስኖ በዓመት ሶስት ጊዜ፣ በተፈጥሮ ዝናብ አንድ ጊዜ በማምረት ከመቶ ኩንታል በላይ ማሽላ ያመርቱ ነበር።አርሶአደሩ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ምንም ዓይነት ምርት ባለማግኘታቸው ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው አመራሮች “የመሬቱ ካሳ ይከፈላችኋል መንገዱን የሚሰሩ ማሽኖች ስራ እንዳይፍቱ ተባበሩን” በሚል የማታለያ ቃል ቦታቸውን ካስለቀቁ በኋላ፣ ለሶስት ዓመታት የካሳ ክፍያውን ባለመክፈላቸው በርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ችግር ላይ መውደቃቸውን ቅሬታ አቅራቢው ተናግረዋል፡፡
ሁሉም አርሶ አደሮች የመሬት ማረጋገጫ ህጋዊ ደብተር የያዙ ቢሆኑም የመሬት ልኬታቸው ተመዝግቦና ተፈራርመው ያስረከቡትም ሆነ ያልተፈራረሙት አርሶ አደረች ያለ ካሳ ክፍያ ለዓመታት በመቆየታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ችግር እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ፡፡