የወልድያ ህዝብ የእለት ገቢ የግብር ተመንን ተቃወመ

ሐምሌ ፫ ( ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በወልድያ ትናንት የእለት ገቢን ምክንያት አድርጎ የተጣለውን ግብር ለመቃወም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በወልድያ የስብሰባ አዳራሽ የተገኘ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይም ተቃውሞውን በከፍተኛ ስሜት አቅርቧል።
ወኪላችን እንደገለጸው ህዝቡ ስብሰባ እንዳለ በማወቁ በብዛት የወጣ ሲሆን፣ አዳራሽ በመሙላቱ ስብሰባውን በውጭ ሆኖ እስከ መከታተል ደርሷል።
ህዝቡ “ እኛን ገድላችሁ፣ ማንን ልትገዙ ነው? ዜጎችን ከስደት እንቀበላለን ትላላችሁ፣ እኛን ደግሞ እንድንሰደድ ትገፉናላችሁ፣ ጦርነት ግጠሙን እያላችሁን ነው፣ እኛ በጥርሳችን እናንተ በጠመንጃ ጦርነቱ ሊጀመር ነው” የሚሉና ሌሎችንም የተቃውሞ ንግግሮችን አሰምተዋል።
የስብሰባው መሪዎች ፣ ጭብጫባ እንዲቆም ቢወተዉቱም፣ ተሰብሳቢዎች ግን በጩኸትና በጭብጨባ የተናጋሪዎችን ሃሳብ በመደገፍ፣ ውትወታውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
የጀበና ቡና ሻጮች፣ ጉልት ሰርተው ፍራፍሬ የሚሸጡ የእለት ፍጆታቸውን መሸፈን ያልቻሉ ነጋዴዎች፣ የቀን ገቢያቸው በ500 ብር፣ ጸጉር አስተካካዮች ደግሞ በ 1 ሺ ብር ተሰልቶ ግብር እንዲከፍሉ ይደረጋሉ።
የቀን ገቢን ታሳቢ ያደረገው የግብር ስሌት በአዲስ አበባ ነጋዴዎች ዘንድም ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል። አንዳንድ ነጋዴዎች የተጣለባቸውን እዳ ሲሰሙ፣ ራሳቸውን መሳታቸውን፣ ሌሎች ደግሞ የንግድ ፈቃዳችንን መልሱልን እያሉ ሲለምኑ ታይተዋል። ማመልከቻዎችን በመያዝ በየቢሮው የሚንከራተቱ ነጋዴዎችን ማየት የተለመደ መሆኑን የሚገልጸው ዘጋቢያችን፣ ባለስልጣናቱና ሰራተኞች ነጋዴዎችን የሚያስተናግዱበት መንገድም እጅግ አስከፊና ሌላ ምሬት የሚፈጥር ነው ብሎአል።
አንድ ነጋዴ ለኢሳት እንደገለጸው፣ ግብር ገማቾቹ በእርሱ የንግድ ድርጅት ላይ ለ6 ወራት ጥናት አድርገው ክፍያውን እንደተመኑበት እንደነገሩትና እሱ ደግሞ ድርጅቱን ከከፈተው ገና 5 ወሩ መሆኑን ቢገልጽላቸውም ሰሚ አላገኝም። ዛሬ ግብር መክፈያ የሚጀመርበት ቀን ቢሆንም፣ በርካታ ነጋዴዎች “ የሚመጣውን እናያለን” በማለት ወደ ግብር መክፈያ ቦታዎች አልሄዱም።