በአዳማ ከተማ የመኪና አደጋና የአስተዳደር ችግር ተባብሰው ቀጥሎአል

ግንቦት ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከተማዋ ውስጥ ያሉት ነባርና አዲስ የትራፊክ መብራቶች ከአምስት ዓመት እስከ ሁለት ዓመታት ድረስ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸው ለትራፊክ አደጋዎች መበራከት ከፍተኛውን ድርሻ መውሰዱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።የፈረስ ጋሪን ቦታ የተኩት ባጆች ለብቻ የሚጓዙበት መንገድ አለመሰራቱም ለመንገዶች መጨናነቅና ለተደጋጋሚ የመኪና አደጋ መከሰት ተጨማሪ ምክንያት ሆነዋል።

ከተማዋ በየጊዜው ከንቲባዎችን ቀያይራለች። ከኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የተሾሙት አዲሷ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሙስናን እንደሚያጠፉ፣መልካም አስተዳደርን እና ልማትን እንደሚያመጡ ቃል ቢገቡም ምንም የተለየ ስራ አለመስራታቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ነዋሪዎች እንዳሉት ከከተማዋ የሕዝብ ብዛት ጋር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በበቂ ሁኔታ የሉም። ወጣቶችን በማደራጀት ተጀምረው የነበሩ የኮብል ስቶን ማንጠፍ ሥራዎች ምክንያቱ ሳይታወቅ ተቋርጠዋል። የመብራት እና የንጹህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎቶችም በተገቢው መንገድ ለነዋሪዎቹ አይደርስም። በተጓዳኝ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ዙሪያ መሬት ሽያጭ ለጊዜው የታገደባቸው ባለስልጣናት፣ ፊታቸውን ወደ አዳማ፣ አደአ፣ ሞጆ እና አካባቢው ወዳሉ ከተሞች አዙረዋል። በዚህም ምክንያት በአዳማ ዙሪያ ለዘመናት ነዋሪ የሆኑ ዜጎችን አፍራሽ ሃይል በማሰማራት እያፈናቀሉ የመሬት ቅርምቱን እንዳባባሱት ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
በተለይ የከተማዋ ወጣቶች ለፍተኛ የስራ አጥነት ችግር መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።