ኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬት ለሱዳን ለማስረከብ ዝግጅት መጨረሷ ታወቀ

ግንቦት ፲፯ ( አሥራ ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በአካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሃይሎችን እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩትን ለመግታት በሚል በሁለቱ አገራት የጋራ ጦር የተቋቋመው ወታደራዊ እዝ፣ ሰፊ የሆነ የኢትዮጵያን ግዛት ለሱዳን ለማስረከብ እንቅስቃሴ ጀምሯል። የጋራ ጥምር ጦሩ በኢትዮጵያ አርሶአደሮች በኩል ሊቀርብ የሚችለውን ማንኛውንም ተቃውሞ ለመጨፍለቅ በዝግጅት ላይ ነው።
ሰሞኑን የእርሻ መሬቱን ለማስረከብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለከቱ ሲሆን፣ በሱዳኖች በኩልም መሬት የመረከቡ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።
ገዢው ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማንኛውም አይነት ተቃውሞ እንዲደረግ የከለከለ በመሆኑ፣ አጋጣሚው አወዛጋቢ የሆኑና በአገር ክዳት ወንጀል የሚያስጠይቁ ውሳኔዎችን ለመፈጸም እየተጠቀመበት ነው። ለአመታት ኢትዮጵያውያን ሲቃወሙት የነበረውን የአገሪቱን ሰፊ የእርሻ መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ከዚህ የበለጠ አጋጣሚ የለም በሚል የህወሃት አገዛዝ የጀመረው እንቅስቃሴ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ዘላቂ የሆነ ውዝግብ እንደሚጠፈር ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
የገዳሪፍ አስተዳዳሪ የሆኑት ሚርጋኒ ሳሊህ ሳኢድ አህመድ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የሚያርሱት መሬት ለሱዳን ለማስረከብ እንቅስቃሴ መጀመሩን አረጋግጠዋል። የመሬት እርክክቡ የሚፈጸመው ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት በ1996 ዓም በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት ሲሆን፣ የሱዳን ገበሬዎች መሬቱን በያዝነው የመኸር ወቅት ተረክበው ወደ እርሻ እንደሚገቡ አገረ ገዢው ተናግረዋል።
የመሬት ርክክቡ በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያንና የአካባቢውን ሰላም የሚያናጉ ቡድኖችን በጋራ ለመውጋት ያስችላል ያሉት ባለስልጣኑ፣ ሁለቱ አገራት ያቋቋሙት ጥምር ጦር ፣ የነጻነት ሃይሎችን ለማጥቃትና የመሬት ርክክቡን ለማስፈጸም መሆኑን ቀደም ሲል በኢሳት የቀረበውን ዘገባ አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ በኩል ግን ጥምር ጦሩ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ተብሎ እንተቋቋመ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፣ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም ይህንኑ ተቀብለው መረጃውን ሲያሰራጩት ቆይተዋል።
የሱዳን አርሶአደሮች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን ሃይሎች እንቅስቃሴ እንዲጠቁሙ ተነግሯቸዋል። የህወሃት አገዛዝ መሬት የማስረከቡን እንቅስቃሴ የጀመረው ከሱዳን ጋር ያለውን ወዳጅነት በማጠናከር ሱዳን ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መንቀሳቀሻ ቦታ እንዳትሆን ለማድረግ ነው።
በኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ የእርሻ መሬት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ ነው።