ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በ1 አመት ከስድስት ወር እስር ተቀጣ

ግንቦት ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን በአንድ አመት ከስድስት ወር እንዲቀጣ የወሰነበት ሲሆን፣ ጌታቸው የእስሩን ጊዜ የጨረሰ በመሆኑ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ሊፈታ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛ ጌታቸው የወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 257 ሀ እና መ ን በመተላለፍ ህዝቡን ለአመጽ በማነሳሳትና በማዘጋጀት ጥፋተኛ ብሎታል።
ጋዜጠኛ ጌታቸው፣ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን ደግፏል ፣መረጃዎችን ለኢሳትና ለግንቦት7 ሲያቀብል ነበር የሚል ክስ ተመስርቶበት ነበር። ጌታቸው የቅጣት ማቅለያ ንግግር እንዲያቀርብ ሲጠየቅ፣ ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም፣ የማቀርበው ማቅለያም አይኖርም ብሎ ነበር።
አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተካራካሪ ድርጅተ ( ሲፒጄ ) እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላልፉን ማውገዛቸው ይታወቃል።