ህዳር 30 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በመዲናይቱ በሚገኙ ትላልቅ ፎቆችና ዋና ዋና መንገዶች ዙሪያ የፌደራል ፖሊስ በመባል የሚታወቁት ተወርዋሪ የጥበቃ ኃይሎችና የደህንነት አባላት ሩጫ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ እየታየ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ዘገባ፤የፌደራል ፖሊሶቹ በየመንገዱ ዜጎችን በማስቆምና “ተለጠፍ“ በማለት ልዩ ፍተሻ እያደረጉ ይገኛሉ።
የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በየቤታቸው በሚመጡ ሦስት የፌደራል ፖሊስ አባሎች ልዩ ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑን የገለጹት የዐይን ምስክሮች፤ ትውልደ- ኢትዮጵያውያኑ፦” ከየት መጣህ? ለምን መጣህ?፣ መቼ ትመለሳለህ?፣ ምን ያህል ጊዜ ትቆያለህን?”የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡላቸው ገልጸዋል።
ትውልደ-ኢትዮጵያውያኑም እነኚህንና መሰል ጥያቄዎችን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ተጠይቀው እንደነበርና አሁን ድጋሚ መጠየቃቸው ለምን እንዳስፈለገ ቤተሰቦቻቸው ቤት ድረስ በመምጣት ለፈተሿቸው የፌደራል ፖሊሶች ቢጠይቁም፤ “ለደህንነት ነው” የሚል ምላሽ ብቻ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
ይህ የውጭ ሀገር ዜግነት ባላቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደረገው ልዩ የቤት ለቤት ፍተሻ ሰሞኑን ከ100 በላይ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ መሪዎችንና አባላትን፤ እውቅ ግለሰቦችንና የውጭ ሀገር ዜጎችን ለእስር ከዳረገው አዲሱ የ”ሽብርተኝነት” ዜማ ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
በቅርቡ ስራ ላይ የዋለውና “አየር እንዳትተነፍሱ”ብቻ ማለት የቀረው አዲሱ የፀረ-ሽብር ህግ ፤ማንኛውም ዜጋ በቤቱ የሚያኖረውን እንግዳ በሚመለከት ለቀበሌ ወይንም ለወረዳ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ያስገድዳል