አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ እና ብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ውህደታቸውን አጽድቀው አንድ ውህድ ፓርቲ በመመስረት የፓርቲ ሊቀመንበር እንደሚመርጡ አስታወቁ

ህዳር 30 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-አንድነት ፓርቲ  ቅዳሜ እና  እሁድ በዲአፍሪክ ሆቴል 2ተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሂድና ውህደቱን የሚያጸድቅ ሲሆን ፣ ብርሃን ለአንድነት ፓርቲ ደግሞ እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዶ የፓርቲው ህልውና ይከስማል

በአዲሱ አንድነት ፓርቲ ውስጥ የፓርቲው ሊቀመንበር በቀጥታ በጠቅላላ ጉባዔ የምረጣል። የፓርቲውን ካቢኔ መርጦ በብሄራዊ ምክር ቤት ይሁንታ አስጸድቆ የሊቀመንበሩም ሥልጣን በብሄራዊ ምክር ቤቱ ቁጥጥር ሚዛናዊ ይሆናል ሲሉ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አባል መናገራቸው ታውቋል፡፡

አዲሱን ውህድ ፓርቲ በሊቀመንበርነት ለመምራት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ እና ዶ/ር ንጋት አስፋው ራሳቸውን ለእጩነት አቅርበው የምረጡኝ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ሲሆኑ፣  የፓርቲው የዜና  ምንጮቻችን ሦስቱም የብዙሃኑን ድጋፍ ለማግኘት በመጣር ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ በቅርቡ ያሻሻለውን የፓርቲውን መርሃ ግብርና ደንብ ያጸድቃል፣ ከብርሃን ለአንድነት ጋር ውህደቱን ይፈጽማል፣ በመድረክ ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ስድስት ፓርቲዎች አንድ ጠንካራ ግንባር የሚፈጥሩበትን ጅማሬ ያበስራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡