ከኢትዮጵያ ተዘርፎ በውጭ አገር ባንኮች የተቀመጠው 11 ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ እንዲመለስ አንድ ታዋቂ ምሁር ገለጡ

ህዳር 30 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-አካውንቲግና የፋይናንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሚንጋ ነጋሽ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጡት፣ በህግ፣ በወነጀል ምርመራ እና በተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህን ገንዘብ ለማስመለስ በአንድነት ሆነው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ።

ችግሩ በአንድ በኩል መንግስት በፖለቲካውና በንግዱ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ የፈጠረው መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ሚንጋ፣ ሌሎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዋነኝነት የሚያሽከረክሩት ኢፈርትና የሸክ አላሙዲ ድርጅቶችም ሊመረመሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የቀረበው ጥናት በዝርዝር ማን ምን ያክል ሀብት እንዳለው እንደሚያመለክት የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፣ ጉዳዩ ከወንጀል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ገልጠዋል።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ይፋ ባደረገው ቅድመ ጥናት መሰረት በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2002 እስከ 2009 ባሉት 7 አመታት ውስጥ፣ ከ187 ቢሊዮን ብር ወይም 11 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገንዘብ ተዘርፎ በውጭ አገር ባንኮች ተቀምጧል።

በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2002 ዓም፣ በአንድ አመት ብቻ ከኢትዮጵያ የተዘረፈው ገንዘብ 3 ቢሊዮን 260 ሚሊዮን ዶላር ወይም 55 ቢሊዮን ብር እንደሚጠጋ መዘገባችን ይታወሳል።

በ2002ዓም ከኢትዮጵያ የተዘረፈው ገንዘብ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በ2001 ዓም ለመደበኛ፣ ለካፒታልና ለክልሎች ድጎማ መድቦት ከነበረው የ54 ቢሊዮን ብር በጀት ጋር ሲነጻጻር፣ የአንድ ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቶአል።

ከ1993 እስከ 2002ዓም ባሉት አስር አመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ የተዘረፈው አጠቃላይ ገንዘብ መንግስት በያዝነው 2004ዓም ከመደበው 117 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር በ60 ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቶአል።

የተዘረፈው ገንዘብ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ውስጥ የገነባቻቸውን መንገዶች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ጤና ኬላዎች ከሶስት እጥፍ በላይ በሆነ መጠን ለማሳደግ ያስችል ነበር።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፣ ከኢትዮጵያ በአለፉት 10 አመታት የተዘረፈው ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ በምግብ ለስራ ፕሮግራም የታቀፉትን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣  ከ4 ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉትን ወገኖች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ወድቀው በቆሻሻ ገንዳዎች ላይ ምግብ እየለቀሙ የሚኖሩትን ዜጎች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ማስቻል ይቻል እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ህብረሰተቡን እያስመረረ ያለው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስ እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሙስና ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተዘፍቀው ገንዘባቸውን በውጭ አገር ባንኮች በማስቀመጥ ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ጥቂት የህወሀት ጄኔራሎችና ባለስልጣናት ናቸው።

አብዛኛው ዘረፋ የተካሄደው ከምርጫ 97 ወዲህ ሲሆን፣  አሁንም ድረስ ተጡዋጡፎ መካሄዱን የፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ዘገባ ያመልክታል።