የፌዴራል ፖሊስ በ11ኛው የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ላይ ሲሳተፉ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን በርካታ ወጣቶች በዋስ መፍታት ጀመረ

ህዳር 30 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:- የፌዴራል ፖሊስ በ11ኛው የኢትዮጵያ ታላቁ የጎዳና ሩጫ   ላይ ሲሳተፉ በቂርቆስ፣ በቦሌ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ፖሊስ ጣቢያዎች በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን በርካታ ወጣቶች ከማክሰኞ ህዳር 26 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በዋስ መፍታት ጀመረ

እሁድ ህዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ታላቁ ሕዝባዊ ሩጫ ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቃውሞዎችን በመንግሥት ላይ አነሳስታችኋል ተብለው በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በቂርቆስ፣ በቦሌ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከሦስት መቶ በላይ ወጣቶች ናቸው።

አብዛኛዎቹ በዕለቱ አመሻሽ ላይ በምክርና በተግሳጽ የተለቀቁ ሲሆን የተወሰኑት ግን እስከ ትላንት ድረስ አልተለቀቁም ነበር ሲሉ ሥማቸውን ለመግለጽ ያልፈቀዱ አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር ለሪፖርተራችን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በታላቁ ሩጫ ላይ መንግሥት ን የመቃወም አድማ አነሳስተዋል በሚል በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ወጣቶች ላይ ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት የሚል ክሥ ሊመሰርት ሞክሮ ነበር ያሉን ምክትል ኢንስፔክተር ፤ ነገር ግን ውሃ የሚቋጥር ተጨባጭ ማስረጃ በመጥፋቱ ታላቁ ሩጫን በመጠቀም እረብሻ መፍጠር፣ የሩጫ ውድድሩን ላልታሰበለት ድብቅ ዓላማ መጠቀም እና ሁከት መቀስቀስ የሚሉ ክሶች ለማቅረብ ተገዷል።

ከማክሰኞ ጀምሮ የክፍለ ከተሞች የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እስከ ትላንት ድረስ ታሳሪዎችን ወጣቶች በዋስ እንዲፈቱ አድረገዋል ፡፡

ማክሰኞ ዕለት የተሰየመው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ካቆያቸው 28 ወጣቶች ውስጥ 27 ወጣቶችን በዋስ የለቀቀ ሲሆን አንደኛውን ተጠርጣሪ ወጣት ግን ፖሊስ “እጁ ላይ መንግሥትን የሚቃወሙ በርካታ መፈክሮችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ፣ አሁንም ከወጣቱ ጀርባ እነማን እንዳሉ በማጣራት ላይ እገኛለሁ” በማለቱ ፍርድ ቤቱ ለማክሰኞ ታህሳስ 3 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በዕለቱ የፌዴራል ፖሊስ በተጠርጣሪ ወጣቶቹ ላይ ያሉኝን ምሥክሮች በሙሉ አላሰማሁምና ጊዜ ቀጠሮ ይሰጥልኝ በማለት ቢጠይቅም ፣ ፍርድ ቤቱ የተሰጠው ጊዜ ከበቂ በላይ ነው፣ ነገር ግን ፖሊስ መረጃ አለኝ የሚል ከሆነ በማንኛውም ጊዜ ክሥ ሊመሰርትባቸው እንደሚችል በመግለጽ በዋስ እንዲፈቱ ብይን ሰጥቷል፡፡