ኢሳት (መጋቢት 7 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ድንበርን ዘልቀው በጋምቤላ ክልል ጥቃት የፈጸሙ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች የገደሏቸው ሰዎች ቁጥር 28 ደረሰ።
ወደ 1ሺ አካባቢ የሚጠጉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በክልሉ ጎግ እና ጆር ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ለተከታታይ ሶስት ቀናቶች በፈጸሙት በዚሁ ጥቃት ታፍነው የተወሰዱ ህጻናት ቁጥርም 43 መሆኑን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ጋዜጣ የክልሉ ቃል አቀባይ ቶል ቻኒን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ማክሰኞ በሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫን ሰጥተው የነበሩት የመንግስት ቃል አቀባይ ዶር ነገሪ ሌንጮ የሙርሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 18 የሚሆኑት ሰዎች መገደላቸውንና 30 የሚሆኑ ህጻናት ታግተው መወሰዳቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና የክልሉ ባለስልጣናት በጥቃቱ በትንሹ 28 ሰዎች ተገድለው ወደ 43 አካባቢ የሚሆኑ ህጻናትም ታፍነው መወሰዳቸውን አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በበኩላቸው የመከካከያ ሰራዊት በአካባቢው የሚስተዋሉ የጎሳ ግጭቶችን ለመቆጣጠር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተሰራ ነው ሲሉ ረቡዕ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ግጭቶችን ለመቆጣጠርና ቁጥጥርን ለማጥበቅ የድልድይ ግንባታ እየተከናወነ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይሁንና የመሰረት ልማት ግንባታው እንስኪጠናቀቅ ድረስ ነዋሪዎቹን ከቀታይ ጥቃቶች እንዴት መከላከል እንደሚቻል አቶ ሲራጅ የሰጡት መረጃ የለም።
ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በድንበር ዘልቀው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በአካባቢው ከ100 በላይ ሰዎችን ገድለው ወደ 125 ህጻናትን ደግሞ አፍነው መውሰዳቸው ይታወሳል።
ታጣቂዎቹ ያገቷቸውን ህጻናት ለማስለቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ድርድር አካሄዶ ወደ 80 የሚጠጉ ህጻናት በሶስት ዙሮች መለቀቃቸውን የተመድ (ዩኒሴፍ) በወቅቱ ገልጿል።
ሰሞኑን ታፍነው የተወሰዱትን ከ40 በላይ ኢትዮጵያውያን ህጻናትን ለማስለቀቅ መንግስት ምን አይነት ዕርምጃ እንደሚወስድ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግን ወደ ጋምቤላ ክልል መንቀሳቀሳቸው ተመልክቷል።
የጎረቤት ደቡብ ሱዳን መንግስት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ትጥቅ ለማስፈታት ለአመታት ጥረት ቢያደርግም ውጤት አለመገኘቱን የሃገሪቱ የፖለቲካ አመራሮች ሲገልጹ ቆይተዋል። ታጣቂዎቹ ጥቃት በሚፈጽሙ ጊዜ ድርድር በብቸኝነት አማራጭ ሆኖ መዝለቁንም ለመረዳት ተችሏል።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሰሞኑን በክልሉ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ቤቶች መውደማቸውን እና የቤት እንስሳትም መዘረፋቸው ታውቋል።
ታጣቂ ሃይሎች ድርጊቱን በምን ምክንያት እንደሚፈጽሙ የሰጡት መረጃ ባይኖርም የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ድርጊቱ የጎሳ ግጭት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሙሩሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደ ጋምቤላ ክልል ለመዝለቅ ጀልባዎችን እንደሚጠቀሙ ለመረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱ ህጻናት በሽምግልና ለማስለቀቅ ጥረት መጀመሩን መንግስት ሃሙስ ምሽት ገልጿል።
እየተካሄደ ባለው በዚሁ የሽምግልና ጥረትም በታጣቂዎች ታግተው ከተወሰዱት ህጻናት መካከል ስድስቱ መመለሳቸውን የመንግስት ቃል አቀባዩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። ባለፈው አመት በተመሳሳይ መልክ ታግተው የተወሰዱ ከ100 በላይ ህጻናትን ለማስለቀቅ መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ሽምግልና በማካሄዱ ህጻናቱ በሽምግልና እንዲለቀቁ መደረጋቸው ይታወሳል።