ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ማሻሻያ አድርገውበት በድጋሚ በስድስት ሃገራት ላይ የጣሉት የጉዞ እገዳ በፌዴራል ዳኞች ታገደ

ኢሳት ( መጋቢት 7 ፥ 2009)

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ማሻሻያ አድርገውበት በድጋሚ በስድስት ሃገራት ላይ የጣሉት የጉዞ እገዳ ለሁለተኛ ጊዜ በፌዴራል ዳኞች ታገደ።

ፕሬዚደንቱ ሃሙስ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ያወጡትን የጉዞ እገዳ የሜሪላንድና የሃዋይ ግዛቶች የፌደራል ዳኞች ውድቅ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፈውበታል።

ፕሬዚደንቱ በድጋሚ ያስታወቁት ደንብ ሃገሪቱን ከሽብር ጥቃት ለመታደርግ ነው ቢሉም የሁለቱ ግዛቶች ዳኞች እገዳው አስተማማኝ አለመሆኑን እና አንድን ሃይማኖት ያነጣጠረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የሜሪላንድ ግዛት የፌዴራል ዳኛ የሆኑት ቴዎዶር ቹአንግ የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር በድጋሚ ያወጡት የጉዞ እገዳ የሙስሊም ዕምነት ተከታዮችን ያነጣጠረ እና የአሜሪካንን ህገ-መንግስት የሚጻረር ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በኢሚግሬሽን ህግ ላይ አጨቃጫቂ ነው የተባለውን ደንብ ሲያርቁ የቆዩት ፕሬዚደንቱ ዳኞች እገዳው በጊዜያዊነት እንዲታገድ ያስተላለፉት ውሳኔ “መጥፎና አሳዛኝ” ዜና ነው ሲሉ ገልጸውታል። በሁለቱ ግዛቶች ውድቅ የተደረገው ጉዳይም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚወሰድ ፕሬዚደንት ትራምፕ ይፋ አድርገዋል።

ከሃሙስ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ታስቦ የነበረው የጉዞ እገዳው የኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ሶሪያና የየመን ዜጎች ለ90 ቀናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ይጠይቃል።

ይኸው ህግ ማንኛውም ስደተኛ ለ120 ቀናት ወደ ሃገሪቱ እንዳይገባ የሚያዝ ሲሆን፣ ፕሬዚደንት ትራምፕ ኢራቅን ያላካተተው መመሪያ ሃገራቸው ከሽብር ጥቃት ለመታደግ ያለመ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል። የአሜሪካው የፍትህ ዲፓርትመንት በበኩሉ ፕሬዚደንቱ አሻሽለው ያቀረቡት የጉዞ እገዳ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዞ እገዳ ውድቅ እንዲደረግ ውሳኔን ከሰጡት የሁለቱ ግዛቶች ዳኞች በተጨማሪ የካሊፎርኒያ፣ የማሳቹሴትስ፣ የኒው ዮርክ የኦሬገንና የዋሽንግተን ግዛቶች በጉዞ እገዳው ላይ ህጋዊ የተቃውሞ እርምጃን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር የጉዞ እገዳውን ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ሲያደርግ የሃገሪቱ የፍትህ አካላት እገዳው የአሜሪካንን ህግ የሚጻረርና አንድን ሃይማኖት ያነጣጠረ በመሆኑ በፍርድ ቤት ውድቅ እንዲሆን ማድረጋቸው ይታወሳል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር ለሁለተኛ ጊዜ አሻሽለው ያወጡት የጉዞ እገዳ ከመጀመሪያው ዙር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው በማለት እገዳው ተግባርዊ እንዳይሆን ዘመቻ ሲያካሄዱ ቆይተዋል።

ፕሬዚደንቱ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስኪወሰዱ ድረስም ከሃሙስ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ታስቦ የነበረው የጉዞ እገዳ ስራ ላይ እንደማይውል ተመልክቷል።