ለልማት ተነሺዎች ተመድቦ የነበረው 100 ሚሊዮን ብር ለግል ጥቅም መዋሉን አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ

ኢሳት ( መጋቢት 7 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ለልማት ተነሺዎች መድቦት የነበረው 100 ሚሊዮን ብር በአመራሮችና በጎሳ መሪዎች ለግል ጥቅም ውሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሃሙስ ለፓርላማ አባላት ገለጹ።

በሃገሪቱ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለፓርላማው የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስሙን መጥቀስ ባልፈለጉት ክልል 100 ሚሊዮን ብር ለተነሺዎች እንዲደርስ ቢመደብም ለግል ጥቅም ውሏል ሲሉ አስታውቀዋል።

አቶ ሃይለማሪያም ይኸው ከፍተኛ ገንዘብ አመራሮችና ተሰሚነት አለን የሚሉ የጎሳ መሪዎች ለግል ጥቅማቸው ስላዋሉት ተነሺዎች የሚገባቸውን የካሳ ክፍያ ማግኘት አልቻሉም ሲሉ ለፓርላማ ገልጸዋል።

መንግስት 100 ሚሊዮን ብሩን ለግል ጥቅማቸው አውለውታል ያላቸውን የመንግስት አመራሮችና የጎሳ መሪዎች በቁጥጥር ስር ያውል አያውል አቶ ሃይለማሪያም የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። መሰል ስህተቶች እንዳይፈጸሙ በቅርበት የሚከታተል ራሱን የቻለ ተቋም በአዲስ አበበ መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ በርካታ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ለልማት ተብለው ቢነሱም ካሳ አልተሰጠንም ሲሉ ተቃውሞን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ለግል ጥቅም ውሏል የተባለው 100 ሚሊዮን ብር ለነዚህ አቤቱታ አቅራቢዎች ሲሰጥ የነበረ ይሁን ሌላው ተነሺዎች የታወቀ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው በኦሮሚያ እና የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ድንበሮች የተቀሰቀሰውን ግጭት እየፈጠሩ ያሉት ሚሊሻ ከሚሊሻ እና ልዩ ሃይል ከልዩ ሃይል ነው ሲሉ አቶሃይለማሪያም ለፓርላማው ገልጸዋል።

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት የጸጥታ አካል የሆኑት ታጣቂዎች ግጭቱን በምን ምክንያት እያካሄዱ እንደሆነና በዚሁ ግጭት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በሁለቱ ክልሎች የነበረው የወሰን ማካለል በአብዛኛው በህዝብ ውሳኔ ተፈቷል ያሉት አቶ ሃይለማሪያም በ26 ቀበሌዎች ግን ችግር መኖሩን አረጋግጠዋል። የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ በአካባቢው ለወራት በዘለቀው በዚሁ ግጭት ከሁለቱም ወገኖች ከ400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮች ከሶማሌ ክልል ሰርገው የገቡ የመንግስት ታጣቂዎች የክልሉን ይዞታ ለመውሰድ እና ንብረትን የመዝረፍ ተልዕኮ እንዳላቸው ይገልጻሉ።

ይኸው ግጭት ዕልባት አለማግኘቱን በቅርቡ ያስታወቀው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በበኩሉ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት ማጣራት እንዲካሄደበትና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም ለፍትህ እንዲቀርቡ ጠይቋል።