የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውበት እንዲቀጥል ተወሰነ

ኢሳት ( መጋቢት 7 ፥ 2009)

ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውበት እንዲቀጥል ተወሰነ።

የጸጥታ ሃይሎች ያለ-ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በጠረጠሯቸው መኖሪያ ቤቶች ላይ ሲያካሄዱ የቆዩት ፍተሻና ብርበራ በአዲሱ ማሻሻያ መነሳቱን ሮይተርስ የመንግስት ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

ህጉ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን አካትቶ አንዲቀጥል ቢወሰንም ለአዋጁ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አልተገለጸም።

አመጽ ያነሳሳሉ የተባሉ የተለያዩ ጽሁፎችንና መልዕክቶችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት በአስቸኳይ የጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል የተወሰነ ሲሆን፣ ይህንን አንቀጽ ምክንያት በማድረግ ግለሰቦች በተለያዩ ድረገጾች ላይ የሚያሰፍሯቸው አስተያየቶችና ጽሁፎች ቁጥጥር ሲደረግባቸው ቆይቷል።

የአዋጁ ተግባራዊነት የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ይህንኑ ጉዳይ መቆጣጠሩን እንዲቀጥል መደረጉን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል። ይሁንና የተለያዩ ጦማሪያንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች በድረ-ገጽ ላይ የሚሰራጩ ጽሁፎችን ማገድና መቆጣጠር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ እንደሆነ ገልጸዋል።

ማሻሻያ ተደርጎበታል በተባለው በዚሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ በመንግስታዊ ተቋማት ስፍራ ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ የተጣለው እገዳም መነሳቱ ታውቋል።

በሃገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መረጋጋት በማሳየቱና አስፈላጊውን የደህንነት ጥበቃ ለማካሄድ አስፈላጊ እንቅስቃሴ በመደረጉ ማሻሻያው ሊተገበር መቻሉን የኮማንድ ፖስቱ ሃላፊ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሲባል መንግስት በጥቅምት ወር አዋጁን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁንና አሜሪካ የአውሮፓ ህብረትና በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አዋጁ የዜጎችን መብት የሚያፍን ነው በማለት ቅሬታን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የዚህኑ አዋጅ ተግባራዊ መደረግ ተከትሎ ከ20ሺ በላይ ሰዎች በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ባለፈው አመት ሃምሌ ወር በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር መንግስት ወስዶታል በተባለ የሃይል ዕርምጃ ከ700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።

መንግስት በበኩሉ በድርጊቱ 500 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጦ ለእስር ከተዳረጉት መካከል አብዛኞቹ ስልጠና ወስደው መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር የሆኑትን ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀለ ገርባን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለህዝባዊ አመፁ ምክንያት ናችሁ ተብለው በክስ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ ለሙሉ አለመነሳት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ስጋት ማሳደሩም ታውቋል።

በጥቅምት ወር 2009 አም ተግባራዊ የተደረገው አዋጅ ለስድስት ወራቶች እንደሚቆይ ተገልጾ እንደነበርም አይዘነጋም።