የካቲት ፳ ( ሃያ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የባህር ዳር ከተማ አዲሱ አስተዳደር ቅዳሜ ከተወሰኑ የከተማዋ ማህበረሰብ ጋር በሙሉዓለም አዳራሽ ባደረጉት ውይይት፣ ከንቲባው አቶ አየነው በላይ፣ “ በከተማዋ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ቢኖሩም የከተማዋ ደህንነቶችም ሆኑ የጸጥታ አካላት ሊደርሱባቸው አለመቻላቸውን፣ ይህም የከተማዋን አስተዳደርና የጸጥታ ዘርፍ አካላት ግራ ከማጋባት አልፎ ማስጨንቁን ተናግረዋል።
በባህር ዳር ከተማ በየጊዜው የተካሄዱት የቦምብ ፍንዳታ ጥቃቶችና ልዩ ልዩ ግድያዎችን አካሄዱ የተባሉ ወንጀለኞች ማንነት ከተማዋን የሞሉት የደህንነት ሰዎች ምንም ፍንጭ ሊያገኙ አለመቻላቸው፣ በደህንነቱ ክንፍ በሚሰሩት ላይ ዕምነት በመታጣቱ ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ ሊካሄድ የነበረው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ እንደተዘዋወረ ከንቲባው በስብሰባው ለተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ ወራቶች በተጠናከረ መልኩ አሰሳ በማካሄድ ወንጀለኞችን ለመያዝ ጥረት ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው የገለጹት ከንቲባው፣ በከተማዋ ውስጥ በርካታ ወጣቶችን በማፈስ በእስር ለማሰቃየት እቅዱ እንዳለ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
በባህርዳር እና በጎንደር ከተሞች በሁለት ሆቴሎች ላይ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙ መዘገቡ ይታወሳል። ለጥቃቱ ሃላፊነት እወስዳለሁ ያለ አካል እስካሁን አልቀረበም።