በኦሮምያና ሶማሊ ድንበር ባለው ግጭት ከ200 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አስታወቀ

የካቲት ፳ ( ሃያ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያና ሶማሊ ክልል አዋሳኝ ድንበር ላይ ባለው ግጭት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከሶማሊ ክልል ልዩ ሃይል ጋር በማበር በባሌ፣ ሳውና እና ቄለም ወለጋ 19 ገድለው 13 ማቁሰላቸውን፣ የኦሮሞ ተወላጆች በወሰዱት የአጸፋ መልስ ደግሞ 35 የፈደራል እና የልዩ ጦር አባላት መገደላቸውን፣ ከ 50 ያላነሱ ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም በጉጂ፣ ቦረና፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሃረርጌ ዞኖች ነዋሪ የሆኑ ቁጥራቸው 200 የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች በጅምላ ሲገደሉ፣ 150 የሚሆኑ ደግሞ ቁስለኛ መሆናቸውን የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የፌደራል እና ልዩ ጦር አባላትን ጨምሮ ከ260 በላይ ሰዎች በአጥቂዎች ወገን መገደላቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
ባለፉት ስደስት ወራት ውስጥ ብቻ በምስራቅ እና ምዕራብ ሃረርጌ ዞን፣ ጉጂ ዞን፣ ምስራቅ ኦሮሚያ፣ ቦረና ዞን እና ባሌ ዞኖች፣ ደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ የተቀነባበረ ግድያዎች ተፈጽመዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ክልሎች ችግራቸውን በሰላማዊ መንገዶች እራሳቸው እየፈቱ ነው ቢልም በሶማሊያ እና ኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የእርስ በርስ ግጭቶችን በማስነሳት ግድያ እየፈፀመ ይገኛል ሲል ክስ የሚያቀርበው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ፣ በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ በፌደራል ሰራዊት እና በልዩ ሃይሉ ጦር የተቀነባበረ እርምጃ እልቂት ሲፈጸም የክልሉ መስተዳድር ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የአገር ሽማግሌዎችን ከመምረጥ ውጪ ግድያው፣ እገታው፣ አስገድዶ መድፈሩ እና ዝርፊያውን አስመልክቶ እርምጃ አለመውሰዳቸውን ወቅሷል።
የፌደራል ወታደሮች በጋንቤላ በኩል አቆራርጠው በወለጋ ቄሌም ዞን አንፊሎ እና ያቲ መንደሮች ውስጥ በመግባት በሽዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀላቸውን እንዲሁም፣ በኦሮሚያ እና ቤኔሻንጉል ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ገዳይ ስኳዶችን በማሰማራት በዜጎች ላይ እልቂት እና ወረራ መፈጸማቸውን አብራርቷል። የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መግፈፍ፣ በጭካኔ መግደል፣ማፈናቀል እና መዝረፍ፣ የእርስበርስ ጦርነቶችን መቀስቀስ ለ አገሪቷ አንድነት ከባድ ተግዳሮት ይፈጥራል ሲል ሊጉ አስጠንቅቋል። የሟቾቹን አሃዝ በተመለከተ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኩል የተባለ ነገር የለም።