በጅንካ ታስረው የሚገኙት የህሊና እስረኞች የረሃብ አድማ ጀመሩ

የካቲት ፳ ( ሃያ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን ከህዳር 4 /2009 ዓም ጀምሮ ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አራት የኅሊና እስረኞች ከ የካቲት 20 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የረሃብ አድማ በማድረግ ላይ ናቸው።
እስረኞች ይህን የረሃብ አድማ ለማድረግ የወሰኑት ከዞን እስከ ፌዴራል ኮማንድ ፖስት ድረስ ጉዳያቸው እንዲታይላቸው፣ በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም፣ እንዲሁም ፓርቲያቸው ጉዳያቸውን ለኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅና አፈጉባኤ አቶ አባዱላ በግንባር የገለጹ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታቸው ነው።
የረሃብ አድማውን በማድረግ ላይ ያሉት ሁለት የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት አመራሮች የሆኑት መምህር ዓለማዬሁ መኮንን ፣ ወጣት ዳዊት ታመነ ፣ የከተማው ነዋሪ አቶ ዘሪይሁን ኢበዞ እና የማጎ ፓርክ ሠራተኛው አቶ አባስ አብዱላሂ ናቸው።
ከአውሮፓ ኅብረትና ከኤምባሲዎች ወደ ዞኑ የተንቀሳቀሱ ኤክስፐርቶች የእነ መምህር ዓለማዬሁን ቤተሰቦች አግኝተው እንዳነጋገሩ ታውቋል፡፡