የኢህአዴግ መንግሥት ከመንግስት ድርጅቶች ሽያጭ በ18 ዓመታት ውስጥ ከ13 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን መረጃዎች አመለከቱ

የካቲት ፳ ( ሃያ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአጼ ሃይለስላሴ እና በደርግ ዘመን ከተገነቡ ፋብሪካዎችና የልማት ድርጅቶች መካከል፣ በቀጥታ ሽያጭ 318 ድርጅቶች፣ በሊዝ 5 ድርጅቶች እንዲሁም 9 ድርጅቶችን ደግሞ በጋራ ልማት ወደ ግል ባለሀብቶች በመዛወር፣ የኢህአዴግ መንግስት ከ13 በሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አስገብቷል።
የመንግሰት ፋብሪካዎች ወደ ግል የማዛወሩ ሂደት ተግባራዊ በተደረገበት በ1987 ዓ.ም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጠቅላላ ቁጥር 234 የነበረ ሲሆን ፣ 593 ሚሊዮን አጠቃላይ ሐብት እንደነበራቸው፣ በሥራቸውም 210 ሺህ 949 የሚሆን የሰው ኃይል ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ድርጅቶቹ አብዛኛዎቹ ተሸጠው በመንግሥት እጅ የቀሩት ቁጥራቸው 25 ገደማ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሲያስተዳድሩዋቸው የነበሩ ሠራተኞችም ዕጣ ፈንታ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውደቁን፣ አንዳንዶቹ ድርጅቶች ከተሸጡ በሃላ በሰበብ አስባብ ሠራተኞችን የማሰናበት ሁኔታ መታየቱና በዚህም ምክንያት ቀላል የማይባሉ አምራች የነበሩ ዜጎች ለችግርና ጉስቁልና መዳረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የፕራይቬታይዜሽኙ ሒደት ከሚተችባቸው መንገዶች አንዱ ድርጅቶቹ የይስሙላ ጨረታ በማውጣት ለሥርዓቱ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት በግዥ ስም እንዲወስዱዋቸው መደረጉ አንዱ ነው፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ከሚነሱት መካከል በፕራይቬታይዜሽን ስም ወደግል ዘርፍ ከተዛወሩ የመንግስት ልማት ድርጅቶች መካከል ከ20 ያላነሱ አትራፊ ኩባንያዎችን በርካሽ ዋጋ መግዛት የቻሉት የሳዑዲ ዜግነት ያላቸው ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አልአሙዲ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሼኩ ከገዙዋቸው ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ ገንዘብ የሚታፈስበት የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን አንዱ ነው።
ንብረትነቱ የብአዴን የሆነውና በነባር ታጋዩ ታደሰ ጥንቅሹ የሚመራው «ጥረት» የተባለው የንግድ ኩባንያ የኮምቦልቻና የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እንዲሁም በከልቻ ትራንስፖርት ማህበር (የቀድሞ የጭማድ ድርጅት አካል) መግዛቱ፣ ህወሃት ደግሞ ኩራዝ አሳታሚ ይባል የነበረውን የመጽሃፍ መሸጫ መደብር፣ የአርባምንጭ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካንና ሌሎችችንም በርካታ ድርጅቶች መግዛቱ ፣ የገዢው ፓርቲ ድርጅቶችና ከእነሱ ጋር በቅርብ የሚሰሩ ባለሃብቶች በፕራይቪታይዜሽን ስም የመንግስትን ተቋማት በርካሽ ዋጋ ወዳራሳቸው ማዘዋራቸውን የሚያሳዩ ናቸው።