ህዳር 25 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኬንያ ምስራቃዊ ክልል የፖሊስ ኮማንደር ማርኩስ ኦቾላ በሞያሌ ቀጣና “አዲ” ተብሎ በሚጠራውና ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰነው የኬንያ መንደር በትንሹ አራት ሰዎች የተገደሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በ ኦሮሞና በ ጋሬ ብሄረሰብ አባላት የተከሰተ ከፍ ያለ ግጭት ወደ ኬንያ በመዛመቱ እንደሆነ በኬንያ ፓርላማ ቀርበው አስረድተዋል።
“ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት በክልላቸው ውስጥ የተነሳውን ግጭት እንዲያስቆሙ ነግረናቸዋል። እኛም ከነሱ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀስን ነው” ብለዋል- ኮማንደር ኦቾላ።
የሞያሌ አካባቢ የፓርላማ ተወካይ አቶ መሀመድ አሊ ግን በግጭቱ አምስት ሰዎች መሞታቸውንና ሰባት መጥፋታቸውን ነው የተናገሩት።
እንደ ገልፍ ታይምስ ዘገባ ፤የተነሳውን ግጭትና በኬንያውያን ላይ የተፈፀመውን ግድያ አስመልክቶ እስካሁን ከኢትዮጵያ በኩል ምንም የተሰጠ አስተያየት የለም።
“መንግስታችን፣ የፀጥታ ሀይሎችና የሞያሌ አካባቢ መስተዳድሮች ሀላፊነታቸውን በ አግባቡ መወጣት ተስኗቸዋል። ችግሩ ባስቸኳይ እንዲቆም ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ፤ ግጭቱና እልቂቱ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ተባብሶ አስከፊ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ፍራቻ አለኝ”ሲሉ አሣስበዋል-የሞያሌው ተወካይ አቶ አሊ።
የአካባቢ ነዋሪዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ኢትዮጵያ ውስጥ በ ኦሮሞና በጋሬ ማህበረሰብ አባለት በተነሳው ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና ግጭቱ ሊቆም አለመቻሉን ተናግረዋል።
ኮማንደር ኦቾላ በበኩላቸው ግችቱን ለማስቆም የኬንያ የፀጥታ ሀይሎች እያደረጉት ያለው የተጠናከረ ጥረት በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ እየጣለ በሚገኘው ዝናም ሳቢያ መደናቀፉን አልሸሸጉም።