ህዳር 22 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ ባለፈዉ እኤአ ጥቅምት 5 2011 የስሎቫክ አምባሳደር ሚላን ዱብቼክን ማሰሯ ስህተት እንደሆነና ወደፊት ተመሳሳይ ድርጊት እንደማትፈፅም የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት በአዲስ አበባ ለሚገኘዉ የአዉሮፓ ህብረት የልኡካን ቡድን በመግለፅ ይቅርታ መጠየቋን የስሎቫክ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
“አሁን የተሰጠንን ማብራሪያና የቀረበዉን ይቅርታ በቂ ሆኖ አግኝተነዋል”” ብለዋል ሚኒስትሩ።
ቀደም ሲል በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ማብራሪያ እንዲሰጥበት ተጠይቆ የሰጠዉ መልስ አጥጋቢ ባለመሆኑ ተቀባይነት ማጣቱን የገለፁት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ነፋስ ለመቀበል ወጥተዉ የነበሩት አምባሳደር ማንነታቸዉን የሚገልፅ አንዳችም ማስረጃ ባለመያዛቸዉ ፖሊሶች ለይተዉ ሊያዉቋቸዉ ያለመቻላቸዉ ለተፈጠረዉ ችግር ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
በተፈጠረዉ ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ወደ ስሎቫኪያ ተጠርተዉ የነበሩት አምባሳደር ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዉ ስራቸዉን እንደሚጀምሩ ሰፔክቴተር ጋዜጣ አመልክቷል።