ኢትዮጵያ፤ ታንዛኒያና ዛምቢያ የቀድሞዉ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን አስረዉ ለፍርድ እንዲያቀርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

ህዳር 22 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በለንደን የሚገኘዉ አለም አቀፉ የሰብኣዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅት አምነስቲ ኢንርተርናሽናል የቀድሞዉ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ለአምስት ቀን ጉብኝት የሚጎበኟቸዉ አገሮች ኢትዮጵያ፤ ታንዛኒያና ዛምቢያ  በሰልጣን ላይ በነበሩበተ ወቅት  ለፈፀሙት አለምአቀፍ ወንጀል አስረዉ ለፍርድ እንዲያቀርቧቸዉ ጥሪ አቀረበ።

ፕሬዝዳንት ቡሽ ለፈፀሟቸዉ ወንጀሎች በቂ ማስረጃዎች በህዝብ፤ በአሜሪካን መንግስት ባለስልጣኖች እና በቡሽ በእራሳቸዉ እጅ እንደሚገኝ  አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባቀረበዉ ጥሪ ላይ ተገልጿል።

“በእስረኞች ላይ በተፈፀመዉ ሰቆቃ ባላቸዉ ሚና ተይዘዉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ቡሽ የሚጓዙባቸዉ አገሮች የማድረግ ግዴታ አለባቸዉ።“ በማለት ማት ፖላንድ የድርጅቱ የህግ አማካሪ አሳስበዋል።

በአፍሪቃ ካለዉ የኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲሁም የማህፀንና የጡት ካንሰር ጋር በተያያዘ ቡሽ የሚያደርጉት የስራ ጉብኝት ያለዉን ዋጋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቢገነዘብም አሰቃቂ ወንጀል በእስረኞች ላይ እንዲፈፀም
መፍቀዳቸዉን ያመኑ ሰዉ በመሆናቸዉ ህጉ በሚጠቅሰዉ መሰረት መጠየቅ እንዳለባቸዉ አስታዉቋል።

በሰዎች ላይ ሰቆቃ የፈፀሙ የትም ተሸሽገዉ ሊያመልጡ እንደማይችሉ አለም አቀፍ ህጉ የሚደነግግ በመሆኑ ኢትዮጵያ፡ ታንዛኒያና ዛምቢያ ይህንን አድል ተጠቅመዉ ጆርጅ ቡሽን ይዘዉ ለፍርድ እንዲያቀርቧቸዉ አስገንዝቧል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለየአገሮቹ የፍትህ ሚኒስቴር መ/ቤቶች አለም አቀፍ ግዴታቸዉን እንዲወጡ በደብዳቤ መጠየቁ ታዉቋል።
የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ተይዘዉ ለፍርድ እንዲቀርቡ አምነስቲ ያነሳዉን ይህን ጥያቄ “ተገቢ ያልሆነ ማስፈራራት“ በማለት አንዳንድ የአሜሪካ በተለይም አብረዋቸዉ የነበሩ የቀድሞ ባለስልጣናት በመኮነን ላይ ይገኛሉ።

በዚህ አመት መጀመሪያ ጆርጅ ቡሽ በስዊዘርላንድ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸዉን የደረሰበት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በተመሳሳይ መንገድ ለስዊዘርላንድ መንግስት የእስር ጥያቄ በማቅረቡ ግብዣዉን ያዘጋጁት
ክፍሎች የጸጥታ ጉዳይን ምክንያት በማድረግ ጉብኝቱ እንዲሰረዝ ማድረጋቸዉ ይታወሳል።

አንዳንድ ወገኖች የኢትዮጵያው ገዢ እራሱ በወንጀል ተፈላጊ መሆኑ እየታወቀ በምን የሞራል ብቃት ጆርጅ ቡሽን እንደሚያስሩ አይተዬንም በማለት በአስተያየት መስጫ ሰሌዳዎች ላይ አስፍረዋል።