የኢትዮጵያ መንግስት ወረራ በረሃብ የተጎዳዉ የሶማሊያ ህዝብ ያለበትን ስቃይ እንደሚያባብሰዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፀ

ህዳር 15 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በሰብኣዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረዉ አለርት ኔት ከናይሮቢ እንደገለፀዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣዉ የሰብኣዊ ሁኔታ ዘገባዉ የኢትዮጵያ መንግስት ወረራ ፣ በረሃብ የተጎዳዉ የሶማሊያ ህዝብ ከመኖሪያዉ እንዲፈናቀልና ህይወት አድን የሆነዉን እርዳታ ትቶ እንዲሸሽ በማድረግ ያለበትን ስቃይ እንደሚያባብሰዉ ገልጿል።

በሶማሊያ 4 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ሲሆን 250 ሺህ ሰዎች ድርቅና የርስ በርስ ግጭት ባስከተሉት ረሃብ የተጎዳ ነዉ።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብኣዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣዉ መግለጫ የረድኤት ድርጅቶች በአካባቢዉ ባለዉ እጅግ የተበላሸ የሰብኣዊ ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ሊያስከትል የሚችለዉ ጉዳት በጣም እንዳሳሰባቸዉ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶማሊያዉ ፕሬዝዳንት ሼክ ሸሪፍ የሚመራዉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሁሴን አረብ ኢሳን የያዘ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በአፍሪቃ ህብረት የኢጋድ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ አዲስ አበባ ተጉዟል።

ኢጋድ የጠራዉ ስብሰባ በአካባቢዉ ደህነንትና በኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያ መግባት ላይ የሚነጋገር እንደሆነ ታዉቋል።

የኢትዮጵያ ጦር በአካባቢዉ ተቀባይነት ስለሌለዉ ይብሱኑ ለተዋጊዎቹ ሚሊሽያዎች ተጨማሪ የህዝብ ድጋፍ እንደሚሰጣቸዉ የሚገመት መሆኑን አለርት ኔት አመልክቷል።