የኢትዮጵያ የካርታ ስራ ኤጀንሲ ብሄራዊ የካዳ-ስትራል ካርታ ለማዘጋጀት ለስራ ተቋራጮች ጨረታ አወጣ

ህዳር 15 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የካርታ ስራዉ የመሬት ይዞታ ድንበሮችን፤ ባለቤትነትና ምዝገባን የሚያካትት ሲሆን ጨረታዉን የሚያሸንፈዉ ድርጅት 23 ከተሞችን፤ የኦሮሚያ፡ የአማራ፤ የትግራይና የደቡብ ክልሎችን ጨምሮ እንዲሁም የቻርተር ከተማ ሆነዉ የተመዘገቡትን የአዲስ አበባንና የድሬዳዋ ከተሞችን በሚሸነሽን መልክ የአየር ፎቶግራፍ ያነሳል።

ከአንድ አመት ጥቂት ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ ከተማ ተመሳሳይ ስራ 50 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ገንዘብ በሚሆን ወጪ በአንድ የጀርመን የአየር የቅያስ ኩባንያ አማካይነት መካሄዱ ሲታወቅ ለዚህ ላሁኑ በሞዴልነት እንደሚያገለግል ታዉቋል።

የአዲስ አበባዉ ፕሮጀክት የምዝገባ ስራ በሚቀጥለዉ አመት እንደሚጠናቀቅ የገለፁት የአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደር የልማት ፕሮጀክት መረጃ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን አምደማርያም በምዝገባዉ መሰረት ለባለይዞታዎች የባለቤትነት ካርታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት 3 አመታት ዉስጥ ይጠናቀቃል በሚባለዉ የካርታ ስራ የኢንፎርሜሽን ኔትወርክ ደህንነት ኤጀንሲ፡ የአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደር መረጃ ፕሮጀክት ጽ/ቤት፡ የትምህርት ሚኒስቴር፤ የኮሙኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የክልል መስተዳድሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት መምሪያ በመሬት ይዞታ፤ አስተዳደር፤ ባለቤትነትና አጠቃቀም ላይ ባወጣዉ መግለጫ ላይ በእንደዚህ አይነቱ የካርታ ስራ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘዉ በፈቃደኛነት ላይ የተመሰረተ የህዝብ አስተያየት እንደሆነ ተገልጿል።

ሕዝብ ተገዶ ሳይሆን ወይንም መንግሰት በፈለገዉ መንገድ ምዝገባ አካሄዶ የሚፈፅመዉ ተግባር ሳይሆን ህዝብ የስራዉን ጠቀሜታ እንዲረዳና በፈቃደኛነት አስመዝግቦ ዋስትና ባለዉ መልክ ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ መደረግ እንዳለበት የአለም የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ያመለክታል።

ግለሰቦችም ሆኑ የአካባቢ ነዋሪዎች በተናጠልና በቡድን ደረጃ ያላቸዉን ፍርሃትና ጥርጣሬ በማያስወግድ መልኩ የሚደረግ አፈፃፀም በአገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚኖረዉ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚገልፁት ጉዳይ ነዉ።

ሕዝብ ሳይወያይበትና በፈቃደኛነት ሳይቀበለዉ እንዲሁም በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሳይመክሩበት በሚቀጥሉት 3 አመታት ዉስጥ ጠቅላላ ስራዉን ለማጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግሰት የሚያደርገዉ ሩጫ ከምን እንደመነጨ ግልፅ አይደለም።

የጠ/ሚር መለስ መንግሰት በጎሳ ደረጃ በሸነሸናቸዉ አካባቢዎች በግጦሽና በሌሎችም የይገባኛል ጥያቄዎች ምክንያት አልፎ አልፎ ግጭቶች ይካሄዳሉ።  አነስተኛ ገበሬዎችን ከይዞታቸዉ እየተፈናቀሉ መሬቶቻቸዉ ለዉጭ ባለሃብቶችና ከበርቴዎች እጅግ በርካሽ አመታዊ ኪራይ የሚቸበችብበት ሁኔታ የአገሪቱ አንድ ችግር ተደርጎ ይቆጠራል።

ከጎንደር ወልቃይት እስከ ታች ጋምቤላ ድረስ ከ1600 ኪሎሜትር በላይ ቁመትና፤ ከ50 ኪሎ ሜትር ያላነሰ የጎን ስፋት ያለዉን የአገሪቱን መሬት መንግስት ለሱዳን አሳልፎ በችሮታ በሰጠበት ሁኔታ ዜጎች በማህበር ተደራጅተዉ በአለም አቀፍ ደረጃ አቤቱታ በማቅረብ ላይ ናቸዉ።

እንዲሁም ነባር የከተማ ይዞታዎች ወደ ሊዝ እንዲገቡ ባለፈዉ ወር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ እንዲፀድቅ መንግስት የወሰደዉ እርምጃ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና በዜጎች ከፍተኛ ተቃዉሞ በሚሰነዘርበትና በሚቀርብበት በዚህ ሁሉ ዉስብስብ የመሬት ጉዳዮች  ባሉበት ሁኔታ ዉስጥ፣  ይህ ያለ ህዝብ ተሳትፎና ስምምነት የሚደረግ የካርታ ስራ ሩጫ አገሪቱን የከፋ ዉዝግብ ዉስጥ ሊከት እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።