የመምህር የኔሰው ገብሬ ሞትን ተከትሎ አንድ ወጣት በአካባቢው ባለስልጣናት ፊት እራሱን በገመድ አንቆ ለመግደል ሞከረ

ህዳር 14 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ህዳር 12 ቀን 2011 ዓም የዳውሮ ዋና ከተማ በሆነው ተርጫ ከተማ የሚኖረው ወጣት እራሱን በገመድ አንቆ ለመግደል የሞከረው፣ የአካባቢው ባለስልጣናት በፈጠሩበት የአስተዳደር በደል ነው።

ለአመቻች መምህርነት  ስራ ለመቀጠር አመልክቶ ምልመላውን አልፎ የነበረው ወጣት፣ ወደ ስልጠና ለመሄድ  ሲዘጋጅ የወረዳው ባለስልጣናት  ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወደ ተጠባባቂነት ቦታ ማውረዳቸውን የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።

በድህነት ይኖር የነበረው ወጣት፣ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ለረጅም ጊዜ ስራ አጥቼ በኑሮየ ተጎድቻለሁ፤ አሁን ደግሞ ችግሬን ይበልጥ የሚያባብስ ነገር ፈጸማችሁ” በማለት የወረዳውን የትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ከወቀሰ በሁዋላ ፣ በጽህፈት ቤቱ ፊት ለፊት እራሱን በገመድ አንጠልጥሎአል።

በስፍራው የነበሩት ፖሊሶችና የአካባቢው ባለስልጣናት ተረባርበው ገመዱን እንደቆረጡትና ወጣቱን ከታነቀበት ዛፍ ላይ እንዳወረዱት የተርጫ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል።

መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት ወጣትም ከሞት ተርፎ በፖሊስ አጀብ ወደ አልታወቀ ቦታ መወሰዱ ታውቋል።

የዋካ ከተማ ተቃውሞ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ከመቼውም ጊዜ በላይ የደህንነት ሰራተኞች መበተናቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በወረዳው የተነሳው ተቃውሞ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች እንዳይሰራጭ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርገው መንግስት፣ ለውጭ አገር የመገናኛ ብዙሀን መረጃ ይሰጣሉ ተብለው የተጠረጠሩት  የመንግስት ሰራተኞች ከስራቸው ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወሩ ወይም ተንሳፋፊ እንዲሆኑ መደረጉን ለማወቅ ተችሎአል።

ሰለሞን ታደሰ፣ ጉብል ጎምበዞ፣  የትናየት ድንበሩና ጌጤነሽ ሸንገፎ የተባሉት የመንግስት ሰራተኞች ከሀላፊነታቸው በማንሳት ወደ ሌላ መስሪያቤት ትዛወራላችሁ በሚል  እንዲንሳፈፉ ተድረገዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የዋካን አመጽ  አነሳስተዋል የተባሉት 12 ሰዎች አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል። እስረኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ  ቢሆንም፣ አቃቢ ህጉ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው በእስር ላይ እንዲቆዩ ተደርጓል።

በዋካ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ  መምህር የኔሰው ገብሬ እራሱን በእሳት አቃጥሎ ከገደለ በሁዋላ ፣ የዋካ ጉዳይ የመላው ኢትዮጵያ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ታውቋል።