ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከክልሉ ተፈናቅለዋል ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች የሚደረገው የገንዘብ መዋጮ ወደ ባንኮችም ተሸጋግሮ ንግድ ባንክ፣ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመስጠት መዘጋጀቱን የባንኩ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ የፊታችን ሃሙስ መቀሌ ላይ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ገንዘቡን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የባንኩ የሩብ አመት ስብሰባ መቀሌ ላይ ለማድረግ ከታሰበ በሁዋላ፣ በአገሪቱ በተነሳው ተቃውሞ ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ በሌሉበት ስብሰባው የተሰረዘ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ስብሰባው መካሄድ አለበት የሚል ትእዛዝ በመስጠታቸው በእለቱ ስብሰባው ይካሄዳል።
ከአማራ ክልል ተፈናቅለዋል ለተባሉ የትግራይ ትወላጆች የተለያዩ ክልሎች ተወካዮች ገንዘብ በማዋጣት ትግራይ ድረስ እየሄዱ ሰጥተዋል። ንግድ ባንክን በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ በረከት ስምዖን ሲሆኑ፣ አቶ አባይ ጸሃየና አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ ዶ/ር ወልዳይ አመሃ፣ ዶ/ር መስፍን በላቸው፣ አቶ ጌታቸው ነጌራና አቶ ነብዩ ሳሙኤል በቦርድ አባልነት ይገኙበታል።