ኢህአዴግ ህዝብን ያረጋጋልኛል ያለውን ሹመት ሰጠ

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ብዙዎች ሹመቱ ምንም ለውጥ የማያመጣ ነው ሲሉ ተችተውታል። በመላው አገሪቱ የሚታየው የለውጥ ፍላጎት  ያስደነገጠው  የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ህዝቡን ያረጋጋልኝ ይሆናል ያለውን እርምጃ ሚኒስትሮችን በመሾም ጀምሯል። የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩት ጌታቸው ረዳ በተሾሙ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከስልጣን በመነሳት የመጀመሪያው ሚኒስትር ሲሆኑ ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም በዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ተተክተዋል።

አቶ መለስ ከሞቱ በሁዋላ የተመሰረቱት የተለያዩ የምክትል ጠ/ሚኒስትር ቦታዎች የፈረሱ ሲሆን፣ የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ቦታውን  አቶ ደመቀ መኮንን እንደያዙት ይቀጥላሉ። አቶ መለስ ዜናዊ ሲሰሩዋቸው የነበሩትን ስራዎች አቶ ሃይለማርያም ብቻቸውን ሊሰሩዋቸው አይችሉም በሚል የተለያዩ ሚኒስትሮችን የሚመሩ ምክትል ሚኒስትሮች ተቋቁመው ነበር።

አዲሱ ሹመት የህወሃት የበላይነት እንደሌለበት ለማሳየት ያለመ ቢሆንም፣ የወታደራዊ ፣  የደህንነትና የፖሊስ ተቋሙ ሳይነካ በመታለፉ አሁንም ሹመቱ የይስሙላ ነው በሚል እንዲተች አድርጎታል። የህወሃት የፖለቲካ አስተሳሰብ እስካለ ድረስ ሰዎችን በመቀያየር የኢትዮጵያን ህዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄ መመለስ አይቻልም በሚል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።