በጢስ አባይ ከተማ ወታደሮች አንድ የጎበዝ አለቃና ሁለት ሴቶችን ገደሉ

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ ያልተለያት የምእራብ ጎጃሟ ጢስ አባይ ከተማ ዛሬ ቀን ላይ ሶስት ነዋሪዎቿ ተገድለውባታል። ከዚህ ቀደም በሁለት የደህንነት አባላት  ላይ ተኩሷል በሚል ሲፈለግ የነበረውን ታፈረ ቢሻው የተባለውን አርሶ አደር ለመያዝ ሙከራ ያደረጉ ወታደሮች ሁለት ሴት ልጆችን ሲገድሉ፣ አርሶአደሩም አንድ የፌደራል ፖሊስ ገድሎ አምልጧል። በዚህ የተበሳጩት ወታደሮች ከወር በፊት በከተማው ተካሂዶ በነበረው ተቃውሞ የጎበዝ አለቃ ሆነው የተመረጡትን አቶ ምክሩ ብርሃኑን ለመያዝ መኩራ ሲያደርጉ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ አቶ ምከሩ አንድ ወታደር ካቆሰሉ በሁዋላ ተገድለዋል። ወታደሮቹ አስከሬን አናስነሳም በማለታቸው የአቶ ምክሩ አስከሬን ለሰአታት አደባባይ ላይ ተጥሎ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አቶ ምክሩ ከሳምንታት በፊት በተደረገው የህዝብ ስብሰባ ላይ “ እኔ ለእዚህ እድሜዬ አልጨነቅም ፣ ራሳችሁን ነጻ ለማውጣት የምትፈልጉ ወጣቶች መደራጀት ትችላላችሁ፣ ቢያንስ አምስት ወጣቶችን ማስታጠቅ እችላለሁ” የሚል ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ የከተማው ህዝብ የጎበዝ አለቃው አድርጎ መርጧቸው ነበር። በአካባቢው ህዝብ ዘንድ በጀግንነታቸው የሚታወቁት አቶ ምክሩ፣ ለህወሃት ከእንግዲህ  አልገዛም  በማለት የአካባቢው ህዝብ ለመብቱ እንዲታገል ሲያስተባብሩ ቆይተዋል።

ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ የአካባቢው አርሶአደሮች በአካባቢው ከሰፈሩት ወታደሮች ጋር በመታኮስ ላይ ናቸው። ሌሊት ሌሊት ተደጋጋሚ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ የታጠቁ አርሶአደሮች መሳሪያቸውን ላለማስረከብ መወሰናቸውንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ቋራ ወረዳ በርካታ ሰዎች ተይዘው ታስረዋል። በሁለት ኦራል መኪኖች የተጫኑ ወታደሮች ዱባባ ቀበሌ በመግባት ነዋሪዎችን ሲያስጨንቁ ውለዋል። ከ4 ያለነሱ ሰዎችንም ይዘው አስረዋል። በምእራብ ጎጃም በፍኖተሰላም ከተማ ደግሞ ህዝቡ ለትግል እንዲነሳ የሚጠይቅ ወረቀት መበተኑን ተከትሎ ወታደሮች ተማሪዎችንና ወላጆቻቸውን እያሰቃዩዋቸው መሆኑ ታውቋል። ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚደረሰውን እንግልት ተቃውመውታል።