(ሃምሌ 22 ፥2008)
የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደ ከፋ ደረጃ ደርሷል በማለት ባለፉት 12 ወራት የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ተቀባይነት ያላገኙ ዳግም ጉዳያቸውን ለማየት መወሰኑ ታወቀ።
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደ ከፋ ደረጃ ደርሷል ሲል የገመገመው የካናዳ መንግስት የኢሚግሬሽን ሚኒስቴር፣ የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ የተደረገባቸው ኢትዮጵያውያን በድጋሚ ማመልከቻ እንዲያስከቡ ጥሪ ማድረጉ ታውቋል።
በኢትዮጵያውያን የፖሊሲ ለውጥ እንደተደረገ የተገለጸው ጥያቄያቸው በካናዳ መንግስት ውድቅ የተደረገባቸው ስደተኞች ከካናዳ በግዳጅ ከመውጣታቸው በፊት ጉዳያቸው እንደገና እንዲታይ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ አይነት የፖሊሲ ለውጥ መደረጉ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱና በስደት ሃገራቸውን ጥለው የወጡ ኢትዮጵያውያን ቢመለሱ አደጋ እንደሚደርስባቸው ውሳኔው በግልጽ ያሳያል ተብሏል።
የህግ ባለሙያው አቶ ተክለሚካዔል አበበ የፖሊሲ ለውጡን በሚመለከት ለኢሳት እንደተናገሩት፣ በካናዳ ህግ መሰረት የዚህ አይነት ውሳኔ 12 ወራት ከመሙላቱ በፊት የማይሰጥ ሲሆን ከዚህ በፊት የጥገኝነት ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ስደተኛ ካናዳን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል” ሲሉ ተናግረው የኢትዮጵያን የፖለቲካ አለመረጋጋት የገመገመው የካናዳ መንግስት ይህን ውሳኔ መስጠቱ ለኢትዮጵያውያኑ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የአለም መንግስታት እና ተቋማት በዜጎች ላይ በሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተወቀሰ ቢገለጽም አለመረጋግታቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየበረታ መሆኑ ይነገራል።
የካናዳ መንግስት ይህንን ተንተርሶ የሰጠው ውሳኔ ሃገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እየገባች እንደሆነ ማሳያ ነው ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።