የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ሃይሎች ላደረሱት ጥፋት ምርመራ ለማካሄድ ፈቃደኛ አይደለም ተባለ

(ሃምሌ 22 ፥2008)

የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የደረሰውን የሰው ሞትና የንብረት ጉዳት አስመልክቶ ግልጽነት የተሞላበት ምርመራ ለማካሄድ ፈቃደኛ አይደለም ወይም በጸጥታ ሃይሎቹ ባህርይ ላይ ምርመራ ለማካሄድ አልቻለም ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ወቀሰ። ጉዳዩ አለም አቀፍ ጣልቃገብነት እንደሚያስፈልገውም ጠይቋል።images

በኦሮሚያ ክልል ከ400 ዜጎች መገደል በሁዋላ እንኳን በመንግስት የተወሰዱ ምንም አይነት ምርመራዎች አለመደረጋቸውን የገለጸው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ የጸጥታ አካላት ሃላፊነት አለመውሰዳቸውንም ሃሙስ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል። በተቃራኒው፣ ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያለው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ የተከሰተውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው በማለት ኮሚሽኑ የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች የፈለጉት ተኩሰው እንዲገድሉ መፍቀዱ አግባብ አይደለም ሲል ተቃውሞ አሰምቷል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሰላማዊ ትግልን የሚያቀነቅኑትን እነ በቀለ ገርባንና አብረዋቸው የታሰሩ ሌሎች ዜጎችን መሰረታዊ መብቶቻቸውን አለማክበራቸው መንግስት ራሱ የፈጸመውን ጥፋት እንኳን ለማስተካከል እንደማይችል አመላካች ነው ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ለቀናት ያካሄዱትን የረሃብ አድማ ተከትሎ ራሳቸውን የሳቱ ሲሆን፣ ወደ ሆስፒታል ሳይወሰዱም የእስር ቤቱ የህክምና ክፍል በእያንዳንዳቸው እጅ ላይ ፈሳሽ ምግብ (ግሉኮስ) እንደተከለላቸው ታውቋል።

የእነ አቶ በቀለ ገርባ መታሰር ለወጣት ኢትዮጵያውያን የሚያስተላልፈው መልዕክት መንግስት ሰላማዊ ተቃውሞን ሽብርተኝነት ማድረጉ ነው ያለው የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ፣ ይህ የመንግስት ድርጊት ግን አገሪቷን ወደ አደገኛ መንገድ እየወሰዳት እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው አትቷል።

በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰውና ከመንፈቅ በላይ በዘለቀው ተቃውሞ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 400 ያህል መሆኑን   እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ፣በአስር ሺዎች መታሰራቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች ከዚህ በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።